ገንዘብ ተልኮልዎታል
የዚህ አሉምኒ ታሪክ መቼም ተነግሮ አያልቅምና ከመካከላችን አንዱ የሆነው ወንድማችን ቀደም ሲል በዚሁ ፕላትፎርም ላይ ያሠፈረውን መልዕክት ጠቅሼ ወደ መጠሁበት ጉዳይ መግባት ፈለግሁ። ወንድማችን የቀድሞ አሥመራ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ሕይወት እንዲህ ሲል ገልፆታል፥ [ትርጉም የራሴ]
"እኔ ነኝ፣ ምክንያቱም እኛ ነን' - ከሦስት አስርት ዓመታት በፊት በዩኒቨርሲቲው የኛ መሪ ቃል ነበር። በባነሮች ላይ አልተጻፈም ነበር፤ ነገር ግን በህይወታችን ውስጥ ተቀርጾ ቀርቷል። ምግብ፣ ልብስ፣ ገንዘብ፣ የጽህፈት መሳሪያ - ችግርን ሳይቀር ተጋርተናል። ድጋፍ ወደ አንዱ ሲመጣ በጸጥታ የሁሉም ነበር። በሁሉም ትግልና ስኬት አንድ ሆነን ቆመናል። ያ የኛ የዝምታ ኮድ ነበር - የማይናወጥ መፈክራችን፥ እኔ ነኝ፣ ምክንያቱም እኛ ነን።"
መቼም ቢሆን የገንዘብ ድጋፍን አንሥቶ የ"ገንዘብ ተልኮልዎታል" ማስታወቂያ ሠሌዳን ምትሀት ሳያነሱ ማለፍ አይቻልም።
"የት ነበር የምትውለው?" የምትለዋን ጥያቄ ማስቀረት ባልችል እንኳን ቁጥሯን ለመቀነስ ስል የውሎን ጉዳይ በቀስታ ነካክቼ አለፍሁት እንጅ በአሥመራ ዩኒቨርሲቲ ቆይታየ ካምፓስ ውስጥ ከማሳልፈው ይልቅ ከካምፓስ ውጪ የማሳልፉው ጊዜ ይበዛ እንደነበር ደጋግሜ አስርግጫለሁ።
ታዲያ አንድ ቀን እንደተለመደው ውጪ ውየ ወደ ካምፓስ (ላሳለ) ስገባ ጓደኛዬን ዋናው በር ላይ - ግብረ ኃይሉን የሚያሳይ መስሎ ቆሞ - አገኘሁት፤ ከሌሎች ጋር። ተገናኝተን ትንሽ እንዳወራን፤ ሁሉንም በመጋበዝ "ዲቲ' ከመጣስ እንግዲህ ወደዚያ አካባቢ "ዎክ" አድርገን ***ላቴሪያ ሻይ ቡና ብለን እንምጣ" አለ ። የራት ሰዓት ተቃርቦ ነበርና "ራት በልተን ብንወጣ አይሻልም?" አልሁ በበኩሌ። "አይ፥ እስኪ ዛሬስ ከዚህ አጠያያቂ የካፌ ምግብ ዞር እንበልለት" አለኝ። ሌሎቹ ደግሞ ያን ሰዓት ከተማ መውጣቱንም አልፈለጉትም ነበር።
በዚህ ሁኔታ ውስጥ እንደገና "ከምሽቱ አራት ሰዓት አካባቢ ስልክ ጠብቅ ተብለሀል" የሚል መልእክት ከካምፓስ የጥበቃ ሠራተኞች ተነገረኝ። ይሁንና ጓደኛዬን ስሜት እንዳልጎዳ በመፍራት እሱ እናምሽ ወዳለኝ ቦታ መሄድን መረጥሁ - ኮምፒሽታቶ ዋናው ፖስታ ቤት አጠገብ ያለው ሆቴል ውስጥ ነን።
ሆቴሉ ውስጥ በርቀት ለማየት እንዲመቼኝ ብዬ ወደ በሩ አካባቢ ያለውን መቀመጫ ብመርጥም ጓደኛዬን አልተመቸውም - ዛሬ ሌላ ነውና ቀኑ። ብዙ ሰዎች ወዳሉበት ጠጋ ብለን ትልቁን ባልኮኔ ደገፍ በማለት ተሰይመናል። ሜሎቲ ቢራ እንደጉድ ይጠጣል። የአሥመራዋ የሆቴል አስተናጋጅ እንደሆነች ሰሜናዊት ኮከብ ነች - ምንም አይወጣላት ታምራለች። በአሥመራ ልጆች ስብዕና፣ ብስለት እና ልግስና ሁለታችንም ያለን አመለካከት ከልክ ያለፈ ነው።
ችግሩ እኔ በተፈጥሮ ወሳኝነት ከአራት ጠርሙስ ቢራ በላይ ገቢ ማድረግ አልችልም። ቀጥሎ ያለው ዕድል ወይ ወደ ጎርዶን ጂን መሸጋገር ወይ ወደ ላሳለ መገስገስ ብቻ። ጓደኛዬ በ11 ቢራ ንቅንቅ አላለም፤ ስለዚህ እኔን ለመያዝ ደብል ደብል ጎርዶን በላይ በላይ ማዘዝ ነበረበት። ጎርዶን ጂን ሲንግል 75 ሣንቲም ደብል ሲሆን ዲስካውንት አለው።
ክምሽቱ 5 ሰዓት። የጦር ሠራዋት መኮንኖች የሆቴሉን አንድ ሰፊ ጠርዝ ይዘው ይዝናናሉ። ወደኛ ሲመለከቱ በጣም ይደሰታሉ፤ የሚሉት ባይሰማንም በፈገግታ ከሩቁ ሲመለከቱን እንደቆዩ ሁለታችንም "ነቄ" ብለናል።
አሁን ሂሳብ ከፍለን መውጫችን ሰዓት ደርሷል። ሰዓት ዕላፊ የማይታሰብ ነው ግን እሱ በፍጥነት እያለፈ ነው።
"ክፈልና እንወጣ ዲቲ" አለኝ ጓደኛዬ።
"ይልቅ አትቀልድ ቶሎ ክፈል፤ ገና አደገኛ አጥር መዝለል ይጥብቀናል" አልሁት።
እንደዚህ ስንባባል ሆቴል ሊዘጋ የእኛን መውጣት ከሚጠባበቁት መሃል አንዷ የሆቴሉ ባለቤት ወይዘሮ ነበሩ። እጅግ በሚገርም ደግነትና አክብሮት "ነገ ትከፍላላችሁ አሁን ወደ ካምፓሳችሁ ሂዱና እደሩ አለዚያም ነፃ አልጋ ይዘጋጅላችሁና እዚሁ እደሩ" አሉን። ጓደኛዬ መንተፍረት ይዞት አላድርም ከማለቱ ሌላ እጮኛው ያሠሩችለትን የጣት ቀለበት እውልቆ በመያዣነት ለሆቴሏ እመቤት ሊሰጣቸው ሲምክር "ዋይ! አንተ ልጅ ምን ሆነህ ነው፤ እግዚአብሔርን አትፈራም እንዴ!?" ተገላቢጦሽ - ደግነት።
ላሳለም ክምሽቱ ሰባት ሰዓት - በጥበቃ ኃይል ባልደረቦች ርህራሄ የተነሳ ገባን፣ አደርን። በሚቀጥለው ቀን በጧት ተነስቼ ወደ ባንክ ቤት ስሄድ ባንኩ የሚከፈትበትን ሰዓት እንኳን ማስታወስ አላስፈልገኝም ነበር።
ትናንት ማስታወቂያ ሠሌዳ ላይ መለጠፉን ያላየሁት፣ ንጉሥ ቀድሞ ያየልኝን "የተላከ ገንዘብ" ለማውጣት ሩጫ።