የኢሠፓ ሚስት ድንገተኛ ፍቅርና ጭንቀት

የማያልቅ የለምና የዩኒቨርሲቲ ት/ት አልቆ ተመርቀን በዕጣ የሀገር ዉስጥ ንግድ ሚ/ር ደርሶኝ ወደ አዲስ አበባ መጣን።እናት ዩኒቨርሲቲያችን በዕዉቀት አንጻን ተመላለሰን እንደምንጠይቃት ቃል አስገብታን በእምባ ሸኘችን።እንደመጣን የ15 ቀን orientation ወስደን ጅማ ተመድቤ ሄድኩ።አዉቶቡስ ተሳፍረን ጉዞ ጀመርን።አጠገቤ ከ30 ዓመት የማትበልጥ ቋንጆ የሚትባል ሴት ናት የተቀመጠችዉ።መተዋወቅ ጀመርን።ተመድቤ ጅማ እየሄድኩ መሆኔን ነገርኳት።እሷ የቤት እመቤት እንደሆነች ነገረችኝ።ባለቤቷ በኢሠፓ ጽ/ቤት ከፍተኛ ባለሥልጣን እንደሆነ ነገረችኝ።ባሏ በጣም አስቸጋሪና እንደሚያሰቃያት አጋራችኝ። ያኔ ተስፋዬ ሰለሰዎች ባህሪ አስተምሮናል መሰለኝ ያለኝን የሳይኮሎጂ እዉቀት በመጠቀም የእንደዚያ አይነት መጥፎ ሰዎችን ባህሪ በመተንተን በመተቸት  ለደረሰባት ጭቆናም ሀዘኔታዬን በመግለጽ ልቧን ቅቤ አጠጣሁ።በቃ ጥሩ ወንድም አገኘሁ ብላ  የሆዷን ሳታስቀር እየነገረችኝ ወልቂጤ ደረስን።እኔም ጥሩ እህት አገኘሁ ብዬ በጨዋነት ረጅሙን ጉዙ ሊናጋምስ ስንል ወልቂጤ ላይ መኪናዉ ተበላሽቷል አልጋ ያዙ ተባለ።ጎን ለጎን አልጋ ያዝን።እራት በልተን ዉሃ ነገር መዉሰዳችንን አላስታዉስም።እሷ ከባሏ ሀሜት ዉጪ ሌላ ነገር እንዲወራ ጨርሶ አትፈልግም ነበር።እኔ እንጀቷን ልበላ እንደሆን አላውቅም የማላውቀዉን ሰዉዬ ከሷ በላይ ጭራቅ አስመስዬዉ እሷኑን ማስደመም ጀመርኩ።ለችግሯ መፍቴሄ የሆንኳት ይመስል ደስ አላት።ሴት ከጠላች አሟጣ ትጠላለች መሰለኝ ትዳርዬዉ እጅ እጅ ብሏታል።ልጆች ነበሯት።እኔም ደግም እሷ አንድ ሲትል ሁለት ከማለት ሌላ አንድም  አስታራቂ ሀሳብ ለማቅረብ አልሞከርኩም።አዉቶቡሱ ተሰብሯል ከተባለ በኋላማ ባሰብኝ።ተፋቺም ሳልላት  እልቀረሁም።እራት በልተን ያንኑን ስናወራ ወደ መኝታ ሄድን።እንቅልፍ እስኪመጣ አንዱ ክፍል እንቆይ ተባባልን።የሷ ክፍል ተመረጠ።እስኳሁን የመጀናጀን ነገር አልተጀመረም።ልቤ ግን መምታት ጀምሯል።የማወራላችሁ የ1981 መጨረሻ ትዝታ መሆኑን አትዘንጉ።ዛሬ መስሏችሁ እንዳትረግሙኝ ብዬ ነዉ።ስንት ዓመት መሆኑ ነዉ? እሷ አሁን ከ65 ዓመት በላይ ይሆናታል አይደለም?

ከአፏ የማይወርደዉ የባሏ ሀሜት ለጅንጀና እንኳ ደቂቃ ሊሰጠኝ አልቻለም።ምናልባት እኩለ ሌሊት ይሆናል መሰለኝ ። አመሰግናለሁ ጥሩ ወንድም አገኘሁ በቃ ሂድና ተኛ አለችኝ።ከዚህ በኋላ የት እሄዳለሁ እዚሁ ተኝተን ሀሜቱንና እርግማኑን እንቀጥልበት እንጂ አልኳት።ወይ ወንዶች  ለካ አንድ ናችሁ።እኔኮ እዉነት ችግሬ ተሰምቶህ መስሎኝ ነበር አንተ ለካ ሌላ ነገር አስበሀሃል አለች።እዉነትም የጨከንኩባት አይነት ስሜት ተሰማኝ።ማሰላሰል ጀመርኩ።ቢቀርብኝስ የሚል ሀሳብ መጣብኝ።ይሄን ያለዉ ልቤ ነዉ።ጭንቅላቴ ደግሞ ወንድ አይደለህም  እንዲትንቅህ ነዉ አሳምናት ይለኛል።ስጋዊ ስሜት አግዞት ጭንቅላቴ ልቤን አሸነፈ።ድካምም እንቅልፍም አለባት መሰለኝ እሷም እየተለሳለሰች መጣች።መኪናዉ ተሰርቶ አደረ ።ጧት ተነስተን የግቤን በረሃ ነካነዉ። ከሰዓት ጅማ ገባን።መ/ቤቴን ከሩቅ አሳይታኝ ዛሬ እዚህ በርጎ አድረህ ጧት ግባ ብላኝ ወደ ቤቷ ሄደች።የሚትሄድበት ጨለማ እየታየኝ በጣም አዘንኩላት።ከእጅ የያዙት  ወርቅ እንደመዳብ ይቆጠራልም አልኩ።

ሰኞ መሰለኝ ቢሮ ገብቼ ተዋዉቄ ሥራ ጀመርኩ። ወዲያዉኑ የቀረቡኝ ያለደመወዝ ልምምድ የሚያደርጉ ሁለት ሴት ልጆች ነበሩ።ነፍሷን ይማርና አንዷ አሁን አርፋለች። የሚወራሁ ስለደመወዜ ትልቅነት ነዉ።500 ብር።ሌሎች ኃላፊዎች ራሳቸዉ እዚያ ስኬል ሳይደርሱ ለጡረታ ተቃርበዋል።ይህ የተጋነነ ደመወዝ ለብዙዎቹ አልጣማቸዉም። አንድ የአሰመራ የኒቨርሲት የ1980 የኢኮኖሚክስ ምሩቅ ከኔ በፊት ተመድቦ እየሠራ ነበር።እየገፉት ሊያብድ ተቃርቧል።አብሮ የሚጎሰም ጓደኛ በማግኘቱ ተደስቷል።ገና እንደገባሁ እሱን በማማት ነዉ የተዋወቁኝ።የከፋፍለህ ግዛ አይነት ነዉ።በቅርቡ ያነበብኳት ጽሑፍ ከመሀይም አትጣላ ብዙ አጋዦች አሉት ትላለች።እዉነት ነዉ።

ቢሮ ሥራ ላይ እያለሁ ያቺ በትዳር ያልታደለች ቆንጆ ከቤት ተነስታ ጥየቃዬ ቢሮ መጣች።የመንግሥት ሠራተኛ ሆኜ በማየቷ ደስ ብሏት ተጫዉተን ሸኘሁአት።አስከሚትወጣ የተጨነቁት እነዚያ ሀለቱ ሴቶች ከሚሰሩበት እየሮጡ መጡ።አንተ ያጓድ እገሌን ባለቤት የት ታዉቃታለህ አለኝ።ዘመዴ ናት አልኩ።ወይዘመድ።እሷ ያዲሳባ ልጅ፡ ምን አገናኛችሁ? ለመሆኑ ቧሏን ታዉቃለሁ?አላውቅም።ጓደ እገሌ ሀገር በሙሉ የሚፈራዉ ነዉ።ይጠጣሃል።በጥዪት ግንባርህን ቢያፈርስ ማንም የማይጠይቀዉ ነዉ።ከዚህቺ ሰዉ ጋር ግኑኝነት ካለህ ነገዉኑ ይሄን ከተማ ለቀህ ብትሄድ ይሻላሃል አሉኝ። ከዚያ ቀን ጀምሮ ፍርሃቴ እየጨመረ መጣ።እንዲያዉ ጌታዬ ፊቷን አታሳየኝ አልኩ።እሷም እነሱን አይታለች መሰለኝ ተመልሳ አልመጣችም።ይሁን እንጂ ገበያ ደርሳ ስትመለስ በጋጣሚ ልሸሽ በማልችልበት ቦታ ፊትለፊት ተገናኘን።ሠላም አልኳትና ከፍርሃት የተነሳ አይኗ ከኔ ጋር እየተንከራተተ ለሥራ ተፈልጌ ነዉ ብዬ ስለሁኔታዋ እንኳ ሳልጠይቃት ሩጫ በሚሰኝ አረማመድ ተለዬሁአት።አንዴ ደግሞ ከሩቅ አይቼአት መንገድ ቀይሼ ተሰወርኩ።የደርግ ሥርዓት ወድቆ አዲስ አበባ መሿለኪያ አከባቢ አግኝቼ ወንድነቴ ተመልሶ ደስ ብሎኝ ሠላም ልላት ሰጠጋት እጇን ዘርግታ ሠላምታ ሊትሰጠኝ እንኳ አልፈለገችም።አይፈረድባትም።ወይ ንቃኝ ወይ ጠልታኝ ወይ ሁለቱም ነዉ ብዬ ትቼአት ሄድኩ።

Previous
Previous

ገንዘብ ተልኮልዎታል

Next
Next

አሰመራ ቤተመንግስት ገብቼ ሊተኮስብኝ ነበር