Staying Alive ah ah...
በ 84/85 አንድ የመስከረም ማለዳ ትንሽ ቀላ ያለ ልጅእግር ወጣት ከአስመራ አውሮፕላን ማረፍያ በሚኒ ባስ ተሳፍሮ ወደ ዪኒቨርሲቲው ሜይን ካምፓስ ሲያቀና ታየ። ያ ልጅ/ያ ሰውዬ ) ሳሙኤል አመሸ የተባለ የማሪን ባዮሎጂ የ88 ምሩቅ ነው ቢባል አሁን ማን ያምናል? ሳሙኤል የያኔ ትዝታውን እንዲህ ያወጋናል ........ የካምፓስ ፖሊሶቹ በመጀመርያ ቀኔ "ፍሬሽ ነህ? - ፍሬሽ ድኻ? ብለው ለጠየቁኝ ጥያቄ በትግርኛ "እወ ፍሬሽ ድየ" ብዬ ጥያቄውንም መልሱንም ቀላቅዬ የዕለት ሳቃቸውን አደልኳቸውና ተፈትሼ ወደ ውስጥ ዘለቅኩ ...አለና ፈገግ ብሎ በትዝታ ፈረስ የኋሊት ጋለበ።.... ፕሮክተሩ ፍትዊ የማደርያ ዶርሜን ሊያሳየኝ በርካታ ቁልፎችን እያቅጨለጨለ የቢሮውን በር ወደኋላው ዘግቶ ወጣ ... ሜዳውን አቋርጠን ከስታዲየሙ ትይዩ፣ የተማሪዎች የልብስ ማጠቢያ የሲሚንቶ ገንዳዎቹን ከበው ከተደረደሩት ዶርሚተሪዎች የመጀመርያውን የብረት በር ከፍቶ አስገባኝ... እነ ሃይለአብ፣ አስፈራቸው፣ ስዩም፣ አጋዚ፣ የአሰቡ አስፋው ወዳጆና ሌሎችም ጋር ተዳብለን አራቷን አመታት እንደቀልድ ላፍ አደረግናት ፦) ... የወጣት ክበቡ የምሽት ድባብ፣ የካፊቴርያው ሰልፍ፣ ድጋሚ ለመብላት ስለምንዘይዳቸው ቴክኒኮች፣ ስለ ቲክ አድራጊው ሙሴ?? ስለ ጋምቤላው የታታ ዙርያ ዘመቻ፣ ስለ ካፌው ሃላፊ ስለ ሰመረ፣ ስለ ተማሪዎች ረብሻ፣ ኧረ ስንቱ ...የቱን አንስቼ የቱን ልተው አለና በትዝታ ነጎደ... "ከሁሉም ከሁሉም" አለ ሳሙኤል ንግግሩን በመቀጠል"ከሁሉም ከሁሉም የተማሪዎች ክበቡ የምሽት ትዝታ በአእምሮዬ ተቀርፆ ቀርቷል። እሱን ላጫውትህ አለና ሊያወጋኝ ተመቻቸ.... አርብና ቅዳሜ ማታ ላይ የተማሪዎች መዝናኛ ክበቡ የእንግሊዝኛ ዘፈኖች ድምቅ ብሎ ይከፈትበትና ያን የሚጣፍጥ የክበብ ሻይ፣ ወይም ለስላሳ እየተጎነጨን፣ በድንግዝግዝ ብርሃን ሙዚቃውን ተከትለው የሚወዛወዙትን ተማሪዎች መመልከት ልማዳችን ነበር - እኔና መሰሎቼ። አንዳንድ ዘፈኖችን የሰማችሁበት ቦታ ከነድርጊቱ ውሳጣችሁ ታትሞ ያውቃል? "Staying Alive" ማለት ለኔ የአስመራ ዩኒቨርሲቲ የመዝናኛ ክበብ ያሳተመው ሲዲ ያህል ትዝታ አስቀምጦብኛል። ምሽት ላይ በክበቡ ውስጥ፣ ልክ ሙዚቃው ሲጀምር፣ ከየጥጋጥጉ ጠረጴዛ ከቦ የተቀመጠ ተማሪ የሚችለውን ያህል አረማመዱን ከሙዚቃው ሪትም ጋር እያቀናጀ፣ አዝናኝ በሆነ መተጣጠፍና መዘረጋጋት፣ ጠረጴዛና ወንበሩን እየገፈታተረ ወደ መሃል ይተማል። ከሁሉም ዳዊትን (ኬሚስትሪ??) ግርም ብሎኝ አየዋለሁ። ዳዊትStaying Alive ሲከፈት ቀድመው ከሚነሱት አንዱ ነው። ቁመቱ አጭር ፀጉሩም ጎፈሬ ነገር ነበር፣ ዝምተኛ ነው፣ አንተዋወቅም .. አሁን የት ይሆን ያለው? በተለይ የዘፈኑ ቤዝ ጊታር ብቻውን ጎልቶ ሲወጣ፣ ዳዊት ከወገቡ ሸብረክ ይልና፣ የሲጋራ ትርኳሽ በእግሩ ጫፍ የሚደፈጥጥ ይመስል በቀኝ እግሩ መሬቱን ጫር ጫር እያደረገ ግማሽ ክብ ሲዞር ሳቂታው ኤልያስ (English) ተስፈንጥሮ ከመቀመጫው ይነሳና ያጅበዋል .... ዓ ዓ ዓ ዓ Staying Alive ዓ ዓ ዓ ዓ Staying Alive ክበቡ ውስጥ ያለው ተማሪ ሁሉ አብሮ ይጮሃል፣ ይዘፍናል። አስቂኝ፣ አዝናኝ ትዕይንቶች በሽ ናቸው ... አንዱ ተማሪ ወገቡን እንደተመታ ድኩላ ከሙዚቃው እኩል እየተንፏቀቀ በአጠገባችን አለፈ፣ .. ወዲያ ላይ ደግሞ አንዱ ትከሻውን ወደላይ በመንፋት እግሩን እንደተሰበረ ሚዳቋ ዝልል ዝልል ሲል ይታየኛል። ዳዊት ምንም ሳይፎርሽ፣ ቀኝ እግሩን ጫር ጫር ፣ ሸብረክ ጫር ጫር እያደረገ ቀጥሏል.... Staying Alive Staying Alive ዓ ዓ ዓ ዓ Staying Alive። አንዳንዶቻችን በትዕይንቱ ተመስጠን ቢቱን ተከትለን ጠረጴዛውን በጣቶቻችን እንጠበጥባለን ...በዚህ ሁሉ ትርምስ መሃል፣ በትልቅ ሰርቪስ ትሪ የሞላችውን መጠጥ፣ በዳንስ የሚውረገረጉት ተማሪዎች እንዳያስደፏት፣ በተማሪዎቹ አናት ላይ ከፍ አድርጋ የያዘችው መልከ መልካሟ የክበቡ አስተናጋጅ ፍሬወይኒ በርቀት ብቅ አለች.... ሙዚቃው እስከመጨረሻው ተከፍቷል ዓ ዓ ዓ ዓ Staying Alive ዓ ዓ ዓ ዓ ጋበዝኳችሁ Staying Alive Staying Alive ዓ ዓ ዓ ዓ Staying Alive