“በደረት መሬት ላይ ተኛ!”
እኔ ቦከናን የማስታዉሰዉ በሁለት ነገር ነዉ። አንዱን ዛሬ ላዉጋችሁ። ሰዓቱ በዉል ትዝ አይለኝም፣ መሸት ሸት ብሏል። በዚያ ምሽት ዶርማችን እያለን ተኩስ የሰማን ይመስለንና ለማጣራት እንወጣለን ( አራተኛ ዓመት ተማሪዎች 2ኛ ፎቅ ላይ ነበርን) ። ከታች ያሉ ተማሪዎች እግር ኳስ ሜዳዉ ላይ በምን ፍጥነት እንደደረሱ ለኛ እንቆቅልሽ ነበር። “እሳት…እሳት” የሚለዉን የተሸበረ ድሞፅ የሰማ ተማሪ ከፎቅ ላይ ያለችዉን ልብስ እና ጠቃሚ የሚላቸዉን ዶክመንት ከነቦርሳዊ ከእሳት ለማዳን ከፎቅ ላይ ቁል ቁል ይለቃል። የተወሰነ ፍርሃት የበረታበት ከፎቅ ለመዝለል ይዳዳል። ታዲያ እግር ኮስ ሜዳዉ ላይ የሰልፍ ትርይት ለማሳየት የተከማቸ የሚመስለዉ ተማሪ በወታደራዊ ቆፍጣና ትእዛዝ “በደረት መሬት ላይ ተኛ” ተብለዉ ሜዳዉ ላይ ተዘርረዉ ከላይ ማየት ቻልን። ታዲያ ያ ወታደራዊ ትእዛዝ የተሰጠዉ ከተማሪ ቦከና መሆኑ በኋላ አረጋገጥን። ወታደራዊ ስልጠና ነበረዉ ተብሎ ተነገረን። በነገራችን ላይ፣ ያ ሁሉ ግርግር አንዳንዶች እንዳወሩት ሻቢያ ከተማ ዉስጥ ገብቶ ሳይሆን ላሳሌ መግቢያ በር ላይ ካሉ ዶርሞች ትንሽ ቀማምሰዉ የገቡ የአስመራ ልጆች የተላጠ የኤሌትሪክ ገመድ በመጠቀም ሲጋራ ለመሎከስ በተደረገ ጥረት በተፈጠረ የእሳት ብልጭታና ከዚህ የተነሳ የመብራቱ ድርግም ከማለት ጋር የተፈጠረዉ ግር ግር ለዚህ ነገሩ ከተረጋጋ በኋላ ለሳቅንበት ትዕይንት ምክንያት ሆኖ ነበር። ታዲይ ይህን ባስታወስኩ ቁጥር ከኔ በመጠን እጅግ ገዘፍ ብሎ ይታየኝ የነበረዉን፣ ቦከና አስታሳለሁ።