"በሽታ ድንጋጤን ይፈራል"

ገና በ፲፱፻፸፰ ዓ.ም አሥመራን ከረገጥን ስድስት ወር እንደሆነን ታመምኩ። ሀኪሞች የተጠናወተችኝ የወባ ትንኝ እንደሆነች ነገሩኝ፤ መታመሜ ከትምህርት መዘናጋቱ አጋጣሚ ጋር ተዳምሮ የፈጠረብኝ ድንጋጤ ከወባዋ ትንኝ ጋር ተደርቦ እንቅጥቃጤዬን አናጠው። እናም ሦስት ይሁን አራት ቀናት ለሚሆን ጊዜ አሥመራ ሰንበል ሆስፒታል ገባሁ። ዩኒቨርስቲ ምግባችን ማታ ማታ ፖስታ ሲሆን፣ ታመው የሐኪም ማስረጃ ያላቸው ብቻ ተፈቅዶላቸው እራታቸውን ጭምር እንጀራ ይበሉ ነበር። እኔም ሆስፒታል በገባሁ ጊዜ ጓደኞቼ አስፈቅደውልኝ ለእራት እንጀራ ያመጡልኝ ነበር። በሰበብ አስባቡ ማታ ለእራት እንጀራ መብላት መቻል እንደትልቅ ፀጋ ነበር የሚቆጠረው።

ወደ ዋናው የፍርሃት ጉዳይ ስንገባ፣ ሆስፒታል በገባሁ በሁለተኛው ቀን ፍንዳታ የበሽተኛ መኝታ ክፍል (patient ward) አካባቢ ተሰማ። ይህን ጊዜ ከፊሉ በሽተኛ በድንጋጤ ድባብ ተውጦ፣ ከድንጋጤው ሳይላቀቅ ጽኑ ሕመምተኛው ሳይቀር ለበር ቅርብ የሆነው - በበር ፣ በሩ የራቀው ደግሞ ደፉ ዝቅ ባለወ መስኮት ያለ ደጋፊ እየዘለለ ወደ ውጪ ተስፈነጠረ።

ፍንዳታው ያኔ እንደተገመተው ለሰበብ ምቹ በነበረው ሻዕቢያ በኩል የተፈጠረ አልነበረም። በሆስፒታሉ ውስጥ ለጽዳት አገልግሎት የሚውለው የወለል ማጽጃ መሣሪያ ሀይል የሚያገኘው ከታመቀ አየር (compressed air) ነበርና በምን ጉድለት እንደሆነ ባልታወቀ ሁኔታ ይህ በታመቀ አየር የተሞላ መሠሪያ መፈንዳቱ ነበር የቁስቋሶው ሁሉ መጠንሰሻ ምክንያት።

እናም "በሽታ ድንጋጤን ይፈራል" እንዲሉ ቁጥሩ ቀላል የማይባል ታማሚ ከድንጋጤ በመነጨ የስሜት መዋሰብ አልጋውን ጥሎ ሰዉን ገፈታትሮ ያለ ችግር በራሱ አቅም ወደ ውጪ ወጣ። የተፈጠረው ድንጋጤ ፍርሃቱን የገፈፈለትና ሰው ገፈታትሮ ለመውጣት ብርቱ የነበረው ታማሚ ሁኔታው ሲረጋጋ ወደ አልጋው የሚመልሰው ደጋፊ ፈለገ። እውነትም "በሽታ ድንጋጤን ይፈራል" በሚለው ገጠመኝ የበሽታ ስሜቱ ብን ብሎ ጠፍቶ ሁኔታው ሲረጋጋ ከድንጋጤው በፊት የነበረው ቀሳፊ ህመም አፍታም ሳይቆይ የየራሱን በሽተኛ እየለየ ተመልሶ በየአካላቸው ተመሰገ።

መልካም ጊዜ

እግዚአብሔር አገራችንን ኢትዮጵያን ሠላም ያድርግልን።

Previous
Previous

ያልተሸጠው ከስክስ ጫማ

Next
Next

የአደይ እንጀራ