ያልተሸጠው ከስክስ ጫማ

ሁለተኛ አመት (1975ዓም) እያለን አንድ ጓደኛችን ጦር መስመር ያለው መቶ አለቃ የሆነ ወንድሙ የወታደር ጫማ ከስክስ ላከለትና የናዝሬት ልጆች የሆንን አንድ አምስት ጫማውን ልንሸጥና ቪላጆ ጂኒየ ዱቃ ጠላ በምኒሊክ ኩባያ ወደ ሰማይ እያንጋጠጥን ልንጠጣ አስበን ወጣን። አምስታችንም ግምት አምሣ፣አርባ፣ወዘተ እየተመንን ተቃቅፈን በምኞት ስለ ገንዘቡም ተመን፣ስንት ስንት እንደምንጠጣ እየወሰንን በፍቅር ተቃቅፈን በተራ በተራ ያንን BIG ጠረንገሎ ጫማ ተሸክመን ገበያ ደረስን።ከደንበኞቻችን የመጀመሪያው 35 ብር ሁለተኛው 30 ሦስተኛው 24 ቀጥሎም 16 ቀጥሎም 9 በመጨረሻም 4ብር እያለ ኋላም በጥላቻ ጭምር ለጫማ መለጠፊያ ተቀዶ ይሆናል እንጂ እያሉ የምንወዳቸውና የምናከብራቸው ደንበኞቻችን ምኞታችንንና የጠላ ጥማታችንን በአፍጢሙ ደፍተው ተስፋችንን ጭምር አጨለሙት።አዝነን አዝነን አምስታችንና ያ ትልቅ ግብዳ ጫማ ስድስታችን በአንድ በተዘጋ ቤት በር ላይ ተጠጋግተን አረፍ ብለን ቁጭ አልን። ከመካከላችን ጥላሁን ዘውዴ  የሚባለው ጓደኛችን አፉን በእጁ እየተመተመ ግብዳው ጫማ (ስድስተኛው ማለት ነው) ሳይሰማን ሸውደነው እንሂድ ብሎ እያንሾካሾከ አዘዘን።በቃ ግብዳውን ጫማ ያረፍንበት የሰው በር ላይ ትተነው ቀስ እያልን በተራ በተራ እየተነሣን ሣይሰማ ሸውደነው ትተነው አምስታችንም በተለያየ አቅጣጫ ወደ ግቢ እንደተኮራረፍን ገባን።ባይዘዌይ ወደኋላ እየተመለስን ትልቅ ዋጋ የሰጡን ጋ መሸጥ አልጠፋንም። ነገር ግን በወደፊቱ ገበያችን ላይ ጥላ እንዳይጥልብን ፈርተን ነው።

መልካምጊዜይሁንልን!!

Previous
Previous

የገብሬ ፓርቲ

Next
Next

"በሽታ ድንጋጤን ይፈራል"