የገብሬ ፓርቲ
ለማስታወስ እና ለመተዋወስ..
በአስመራ ዩንቨርስቲ ቆይታችን ትዝታዎቻችን ውስጥ አንዱ "የገብሬ ፓርቲ" ነው። ገብሬ የ85 ገቢ የአካውንቲንግ ተማሪ ሲሆን ሙሉ ስሙ ገብረሚካኤል ማኔ ነው። ገብሬ በአመት ሁለት ጊዜ የመዝናኛ ፓርቲ ያዘጋጃል። ዝግጅቱ የሚካሄደው ላሳሌ ካምፓስ ሲሆን ገብሬን የሚያውቅ በሙሉ የመገኘት መብት አለው። ፓርቲው የሚካሄደው የሴሚስቴር ፈተና እንደተጠናቀቀ ነው። ገብሬን የሚያውቅ ሁሉ በፓርቲው መገኘት ቢችልም የሚጠበቅበት ስራ አለ። ለፓርቲው ማዘጋጃ ገንዘብ የማግኛ ስራ መስራት ይጠበቅበታል። አንደኛው" ወረቀት" ሽያጭ ነው። ፈተና ከተጀመረበት እለት ጀምሮ በየክፍሉ ለማሰቢያ የሚሰጠውን ወረቀት ከፈተና በኋላ ተከታትሎ ሰብስቦ ማምጣት፣ የዝግጅቱ አባል በሌለባቸው ክፍሎችም ተዘዋውሮ መሰብሰብና ማጣራቀም አለ።
ተማሪው በሴሚስቴሩ ለማሰቢያ የተጠቀመባቸው ወረቀቶችም ከየዶርሙ ይሰበሰባሉ። በአመቱ መጨረሻ ተማሪዎች ወደቤተሰባቸው ሲሄዱ የሚተዋቸው አሮጌ ጫማዎች ይሰበሰባሉ። "ማን ወረቀት አመጣ፣ አላመጣም? ገብሬ ይከታተላል። ፈተና እንደተጠናቀቀ ሳምንት ሙሉ የተሰበሰበው ወረቀት 'ቦን -ቮየጅ" የሚል ጽሁፍ ባላቸው ቦርሳዎች ወደ ገበያ ተወስደው ይሸጣሉ። የአሮጌ ጫማዎች ሽያጭ 'ገበያውኑ ለሚያውቁት ' ይሰጣል። ፓርቲው መቼ እና ላሳሌ የትኛው ዶርም እንደሚካሄድ ገብሬ ይወስናል። ዶርም ይመረጣል፣ የሚመረጠው ዶርም እስከ ሰላሳ ሰው የሚያስተናግድ ነው። ዶርሙ የማመቻቸት ሀላፊነት በተሰጠው/በተሰጣቸው ተማሪዎች ይዘጋጃል፣ለሀውስ ፋዘር እንዲያውቀው ይደረጋል። የገብሬ ፓርቲ ቀን ከምሳ በኋላ በጫት ነው የሚጀመረው። ከስራ ክፍፍሉ አንዱ የሙዚቃ/ ዘፈን ዝግጅት ነው። የሙዚቃ ማጫወቻ ከየትም-ከየትም ተፈልጎ ይመጣል። በሚቃምበት ሰአት መጀመሪያ የሚከፈተው ሙዚቃ ፣መሀል ላይና ወደ መጨረሻ አካባቢ ከሚለቀቀው ሙዚቃ/ ዘፈን የተለየ ነው።ለዚህም የሚመደብ ሰው አለ።
ወደ አመሻሽ ላይ ሌላ ፕሮግራም ይቀጥላል፣ ሙዚቃ፣ ዳንስ፣ጭፈራ። ወደ ሙዚቃ "ዘው "ተብሎ አይገባም፣ መጠጥ ይቀድማል። በወረቀትና አሮጌ ጫማ ሽያጭ የሚገኘው ገንዘብ ለጫት ብቻ ሳይሆን ለመጠጥ ግዢም የሚውል ነው።
የሚጠጣውን የሚገዛ፣የሚያዘጋጅና የሚያስተናግድ ገብሬ በመደባቸው ይካሄዳል።
የሚጠጣው ' ፓንች' ነው። በብዙ ጠላ እና ቪኖ ድብልቅ የተዘጋጀ። ይጠጣል፣ይጠጣል፣ ይጨፈራል፣ ይጨፈራል። ገብሬ ጥሩ ድምጽ ያለው "ዘፋኝ ወይም አንጎራጓሪ" መሆኑም መጠቀስ የሚገባው ነው። በተለይ የአስቴርን ዘፈኖች ሙሉ በሙሉ ይጫወታቸዋል፣በመቀጠል የሙሀመድ አህመድን። ስለ ገብሬ በጨረፍታ ነው ያቀረብኩት። ስለ እሱ እያሰብኩ ከዚህ በላይ መጻፍ አልተቻለኝም። ገብሬ/ገብረ ሚካኤል ማኔ / አሁን ከዚህ አለም መከራ እና ድካም አርፏል። ፈጣሪ ነብሱን በአጸደ ገነት ያኑራት።