ሀብቴና እስማኤል..
ለማስታወስና ለመተዋወስ.... ይሄ የዋትስ አፕ የማህበራዊ ትስስር ገጽ ብዙዎቻችንን ብቻ ሳይሆን ሁላችንንም እርስ በእርስ እንድንገናኝ አስተዋጽኦው ብዙ ነው። እኔ እራሴ ብዙዎች ጋር ተገናኝቻለሁ፣ ወደፊትም ገና ብዙ ጓደኞቼ ጋር እገናኛለሁ። በብዕር አምባ ፕሮግራም ያቀረብኩት
"ልብሽን አሰሪው ተነቃነቅ በይው፣
ከደም ዑደት ሌላ ማፍቀርን አላምጂው
አፍሽም- ከንፈርሽ ሰለቸው ማላመጥ፣
እስኪ አሁን ደግሞ አላምጂው መመጠጥ
አሳይው መመጠጥ፣መመጠጠጥጥ....."
የሚል ግጥም የጻፍኩላትን ልጅ ገና አላየኋትም፣አላገኘኋትም። አይኔን ከዋትስ አፕ አልነቅልም። ሌሎች ጓደኞቻቸውን በማግኘት እንደቀናቸው ሁሉ እኔም አንድ ቀን አገኛታለሁ። ከጥቅምት 24ቱ ስብሰባ በኋላ እንኳን ስንቶች ተገናኝተዋል መሰላችሁ። ከእነዚህ ውስጥ ግርምት የፈጠረብኝን አንዱን ላውጋችሁ።
አሜሪካ የሚኖረው የእስማኤል ሙሳ እና አዲስ አበባ የሚኖረው ሀብቴ ጀቤሳ (ዶ/ር)። በዚሁ በዋትስ አፕ የተገናኙት በቀደም ማክሰኞ ነው፣ጥቅምት 28/2017 ዓ.ም።" እንዴት ተገናኙ?" ከዋትስ አፕ ላይ ሀብቴ ጃቤሳ የሚል ስም ተመለከተና የድሮው የቅርብ ጓደኛው መሆኑን በመጠርጥር ቁጥሩን ወሰደና ደወለ እስማኤል፣ በእርግጥም የድሮ ጓደኛሞች ተገናኙ።
ታሪኩን ከስሩ የሚከተለውን ይመስላል።
ሀብቴ እና እስማኤል ጓደኝነታቸው ከሁለተኛ ደረጃ ተማሪነት የጀመረ ነው፣ ከዘጠነኛ ክፍል እስከ አስራ ሁለተኛ ክፍል አብረው ነው የተማሩት፣ አብረው ነበር የሚያጠኑትም። ሁለቱም ጎበዝ ከሚባሉት ተማሪዎች የሚመደቡ ነበሩ፣ የሚጠበቁም ነበሩ። እንደተጠበቁትም በአስራ ሁለተኛ ክፍል ፈተና የዲግሪ ትምህርት መቀጠል የሚያስችል ውጤት አምጥተዋል።
የአስራ ሁለተኛ ፈተና ተፈትነው እንደጨረሱ በአንድ ጉዳይ ሁለቱም ለእስር ተዳረጉ። ባሕር ዳር ታሰሩ። የታሰሩበት ምክንያት "መጤ ሐይማኖት ተከታይ ናችሁ" ተብለው ነው። ሁለቱም የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ ነበሩ። እስማኤል ከአምስት ወራት እስር በኋላ ተፈታ። ዩኒቨርስቲ መግባት የሚያስችል ውጤት መጥቶለት ስለነበረ ወደ አሰመራ ዩኒቨርስቲ ሄደ/መጣ ፣ ኢኮኖሚክስ ነው ያጠናው።
እስማኤል ከተፈታ ከአንድ ወር በኋላ ሀብቴም ተፈታ። እሱም ወደ አሰመራ ዩኒቨርስቲ ሄደ/መጣ ናቹራል ሳይንስ ባዮሎጂ አጠና።
እስማኤል ወደ አስመራ ሲመጣ ጓደኛው ሀብቴ አዲስ አበባ ዩንቨርስቲ እንደሚገባ ነው የገመተው። ሀብቴ ወደ አስመራ ዩኒቨርስቲ ሲመጣ ጓደኛው እስማኤል አዲስ አበባ ዩንቨርስቲ እንደሚገባ ነው የገመተው።እስማኤል-ሀብቴን አስመራ ዩኒቨርስቲ ይኖራል ብሎ አልጠበቀውም፣ ሀብቴም እንደዚያው። ሁለቱም አስመራ ዩንቨርስቲ ተቀምጠው አንዱ አንደኛውን አዲስ አበባ ዩንቨርስቲ እንደሚማር እየገመቱ አንድም ቀን ሳይገናኙ የአራቱን አመት ትምህርት ጨርሰው ተመርቀው ወጡ፣የተለያየ ሀገር ተመደቡ። ተለያይተው ቀሩ።
"አራት አመት ሙሉ አስመራ ዩንቨርስቲ ውስጥ እንዴት ሳይገናኙ ኖሩ?" የእኔም ጥያቄ ነው። ካፌ በቀን ሶስቴ እንጠቀማለን። በወር ዘጠና ጊዜ ካፌ እንገባለን እንወጣለን፣በአስር ወር ዘጠኝ መቶ ጊዜ በአራት አመት 3,600 ጊዜ ማለት ነው። ሻይ ቤት በቀን ሁለት ጊዜ እንጠቀማለን ብንል በአራት አመት 2,400 ጊዜ ወጥተናል ገብተናል ። ካፌ እና ሻይ ቤት ብቻ 6,000 ጊዚ ሲወጡ፣ሲጠቀሙ እና ሲወጡ ሀብቴና እስማኤል እንዴት ላይተያዩ፣ላይገናኙ ቻሉ። ላይብረሪም ሌላው መገናኛ ነበር፣ ነገር ግን በእነዚህና ሌሎችም ተማሪዎች ሊተያዩ፣ሊገናኙ በሚያስገድዱ ሁኔታዎች ሳይገናኙ የኖሩት እስማኤል እና ሀብቴ በቀደም በዋትስ አፕ ተገናኙ።
እኔማ አሰብኩ አሰብኩና በተለይ የገጠማቸው እስር ጉዳዩ ተከትሏቸው እንዳይሄድ ከሁለት አንዱ ከጎጃም "አዋቂዎች ዕጸ-መሰውር " አስደግመው ይዘው ይሆን ?" ብያለሁ።
ይህን ታሪክ አንተ እንዴት ልትጽፈው ቻልክ ? ብላችሁ ብትጠይቁኝ "እስማኤል ከሀብቴ ጋር ተደዋውሎ ከተገናኙ በኋላ ወዲያውኑ በግርምቱ እንደተዋጠ ነበር ደውሎ እንድጽፈውና እንድለጥፈው የነገረኝ። "ደነበኛ" አርጎኝ ይመስለኛል፣ ሀብቴም የእስማኤልን "Recommendation " ተቀብሎ ይመስለኛል እንድጽፈው የፈቀደው። የጎደለ፣የተንጋደደ ካለ እንደሚያስተካክሉት እምነቴ ነው።