የ50 ሳንቲም ዶሮ የብር ገመድ ይዛ ጠፋች
እስክርብቶ አልቆብኝ ነገ ምን ይዤ ክፍል እገባለሁ እያልኩ ከላሳሌ ለራት ወደ ዋና ግቢ ብቻዬን ጉዞ ጀመርኩ።አንድ ዘናጭ ጫማ ብቻ ናት የነበረችኝ።አንድ ሌላ አሮጌ ለኔ ብጤ ጓደኛዬ ሰጥቼ ነበር።እሱ ደግሞ ጫማ አልቆበት በስሊፐር መሄድ ጀምሯል።አሁን ዶ/ር ነዉ።በድብርት እየተጓዝኩ እያለ ባርካ ት/ት ቤት ጋ ሲደርስ ወጣቶች መረብ ኳስ ይጫወታሉ።መረብ ኳስን እያዩ ማለፍ ለኔ ከባድ ነበር።ጎራ አልኩ።ስደርስ በሳንቲም ይጫወታሉ።እኔ የምገባበት ቡድን እንደሚያሸንፍ ተረዳሁ።ከሁሉ በላይ የእስክሪብቶ መግዣ እንደማገኝ ተማመንኩ።አንዱ ቡድን ተሸንፎ ሲወጣ አስገቡኝ አልኩ።ገንዘብ አዋጣ አሉኞ።ገንዘብ የለኝም አልኩ።የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ነኝ።ካስገባችሁኝ ግን ታሸንፋላችሁ አልኳቸዉ።ሀዘኔታም ተጨምሮበት አስገቡኝ።የእስክሪብቶ ችግርም ተጨምሮ የተቃራኒዉን ቡድን ቀጥቅጠን አሽነፍን።አንድ ብር ካምሳ ደረሰኝ።ደስታዬ ልዩ ሆነ።እሱ አያስይዝ እንዲሁ ይግባ አሉ።አሁንም በሚያስደመድም ሁኔታ አሸነፍን። የዛኑን ያህል ገንዘብ አገኘሁ።እራት ስለሚያልቅብኝ ልሄድ ነዉ አልኳቸዉ።ፈርምልን ብቻ ነዉ የቀራቸዉ።እባክህን ሁሌ ናና እንጫወት አሉ።ቃል ገባሁላቸዉ።ሶስት ብሬን ይዤ ለራት ሄድኩ።ብዙ እስክሪብቶ መግዛት እንደምችል አረጋገጥኩ።ገዛሁም።ራቴን በልቼ ላሳሌ ስደርስ ግን አንድ አሳዛኝ ነገር ተከስቷል።ጫማዬ ተተርትሯል። ደስታ ወደ ሀዘን ተለወጠ።እግሬ ትልቅ ስለሆነ ለመዋስም አላገኝም ነበር።ማንስ ኖሮት ሊሰጠኝ?ለካ አንድ ጓደኛችን መስፊያና ስባጎ ነበረዉ።ሄጄ ለመንኩት።መሳሪያዎቹን አዉጥቶ በጥሩ ሁኔታ ሰፍቶ ሰጠኝ።ዛሬ የራሱ ፈርም ያለዉ አካወንታንት ነዉ።ዉለታዉን እስከዛሬ ረስቼ አላዉቅም።ወደፊትም አልረሳም።