የሀይሉ በሶ

ለማስታወስና ለመተዋወስ.......

ሽፈራው

 የሀይሉ በሶ

 "ከቤተሰብ በተቋጠረ የደረቅ ስንቅና አጠቃቀም በተመለከተ ምን የተለየ ነገር ፣ ምን ትዝታ አላችሁ?

 ባለፈው ከነገርኳችሁ ከ"ሰሌ" በስተቀር ያመጣውን ዳቦቆሎም ሆነ፣ ቆሎ፣በሶ ወይም ሌላ ደረቅ ስንቆችን መብላት ወይም መጠቀም ለብዙዎች ችግር ነበር።  ያለህን ተካፍለህና አካፍለህ የመብላት "ባህል ና ልምድ" በአንድ በኩል ይስብሀል፣ ይጎትትሀል። መካፈል፣ ማካፈልን ስታስብ ደግሞ በአንድ ዶርም እስከ አስራ አምስት እና ሀያ ተማሪ መኖሩ ችግር ይሆንብሀል። በዚህም ምክንያት የተለያዩ አጠቃቀም ዘዴዎች ነበሩ። የተወሰኑትን፣ ያጋጠሙኝን አንዳንዶቹን ላስታውሳችሁ።

አንዳንድ ተማሪዎች የቋጠሩትን ደረቅ ስንቅ በዶርሙ ውስጥ ያለው ተማሪ አነስተኛ መሆኑን አይተው የሚያወጡ አሉ። እነዚህ ተማሪዎች በተለይ እንደ ዳቦ ቆሎ እና ቆሎ የመሳሰሉትን አውጥተው ትንሽ፣ትንሽ አስቆንጠረው ወይም በጭብጥ-በጭብጥ አዳርሰው፣ አቃምሰው በነጻነት የሚጠቀሙ ናቸው ወይም ነበሩ።  የራሱን ካፖርድ ውስጥ ቆልፎ አስቀምጦ ወደሌሎች የሚያንጋጥጥም ነበረ።  ከሌላ ዶርም ጓደኞቹ ሲመጡ ወይም የአገሩ ልጆች ሲመጡ አውጥቶ ለ "እንግዳዎቹ" ብቻ የሚጋብዙ የሚያቀርቡም ነበረብን/ ነበሩብን። "እንግዳ"ፊት እንደማይጠየቅ በመተማመን።

እነ ቆሎ እና ዳቦቆሎን በኪሳቸው ቀንሰው ከግቢ ወጥተው ኔቪ ድረስ ዎክ እያደረጉ በልተው ጨርሰው የሚመጡም ነበሩ። አንዳንዶች ደግሞ በአንሶላ በሚከለለው አልጋ ውስጥ ገብተው በድምጽ አልባ አቆረጣጠም የሚበሉ እና ሌሊት ሁሉም ከተኛ በኋላም የሚበሉ ነበሩ፣ ነበሩብን፣ነበርን።

እኔ ግን "አንተስ?" አልባልም። እኔና እስማኤል የዚህ መሰል ችግር አልገጠመንም፣ እድሜ ለጌቱ! ያመጣናትን በሳምንት ውስጥ አጠናቅቀን ነጻነታችንን ተጎናጽፈናላ!

*****

የሀይሉ በሶ ልዩ ታሪክ ፣

 ሀይሉ ተስፋዬ የተቋጠረለትን ስንቅ ካፖርድ ውስጥ ቆልፎ በጥንቃቄ የሚጠቀም ነው። የሀይሉ "በሶ" በሶ ብቻ የሚባል አይደለም። በቅቤ የታሸ ሆኖ " ለጭኮነት የቀረበ ነው።  ሀይሉ ብዙ ጊዜ የሚጠቀመው ቅዳሜና እሁድ ጧት ነው፣ ለቁርስ ወደ ሜይን ካምፓስ ላለመሄድ። ሀይሉ ብቻውን መብላት አይወድም፣ ሁሉም ከተኛ በኋላ ሌሊት አውጥተው እንደሚጠቀሙትም አይደለም፣ እንደ ጌቱም አንዴ "እንፍጀውም" አያስማማውም። ምግቡ በራሱ ችግር ፈጣሪ ነው፣ ጭኮ ነዋ!።

እንደ ቆሎ ወይም ዳቦቆሎ ለዶርሙን ሙሉ ማዳረስ አይቻልም። ጌቱ ለዘረጋው የአበላል ባህል አመቺ አይደለም።

"ጧት ቁርስ አንሄድም!" ይለኛል አርብ ማታ። ይገባኛል ቁርሳችንን እዚሁ ጭኮ እንበላለን ነው። ጧት አንድ ጭብጥ ከበላህ እንደሌላው ጊዜ የምሳ ሰአት መድረሱን ሆድህ አይነግርህም።

ሀይሉ ለሴሚስቴር እረፍት አዲሳባ ሄዶ ያመጣው ተጨማሪ ጭኮ "ተተናኳይ" አፈራ። አንዱ የዶርማችን ልጅ የመጀመሪያው ሴሚስቴር ውጤቱ ተበላሽቶበት እዚያው ግቢ መክረም መርጧል። ይሄው ልጅ ጧት ለቁርስ አይሄድም፣ ለእራት እሱ ወይም ከእኛ ውስጥ አንዳችን የምናመጣውን ዳቦ ጧት ለቁርስ በልቶ እዚያው ተኝቶ አርፍዶ ለምሳ ነው የሚመጣው።

አንድ ቀን እንዲህ ሆነ፣

ሀይሉ በምን ምክንያት እንደሆነ አላስታውስም ግን አንድ ቀን ጧት ሀይሉ ሜይን ካምፓስ ደርሶ ተመልሶ ላሳሌ ይመጣል። ዶርም ውስጥ የሚገኘው ይሄው ጓደኛችን ብቻ ነው። ተማሪ ሁሉ ከሄደለት በኋላ ተነሰቶ ተጣጥቦ ጠረጴዛው ላይ የሀይሉን ጭኮ መሳይ በሶ ከነመያዣው አስቀምጦ፣ ተደላድሎ ጭኮውን እያጣጣመ እያለ ነበር ሀይሉ የደረሰው።

ሀይሉን ሲያየው መደንገጥ የማይቀር ነው። ደነገጠ- በድንጋጤ ውስጥ ሆኖ "ፎርስ! ና እንብላ!" ብሎ አብረው እንዲበሉ ጋበዘው።( ሀይሉ ካሉት የተለያዩ ስሞች አንዱ " ፎርስ" ነው።)  ሀይሉ ያመጣው በሶ/ጭኮ በሮዝማን ሲጋራ የማስታወቂያ ፌስታል ነው። በግምት አርባ ሳንቲ ሜትር ቁመት ባለው ፊስታል የተቋጠረው በሶ/ጭኮ ጠረጴዛ ላይ ቀጥ ብሎ የሚቆም ነበረ። ከወር በማይበልጥ ጊዜ የተጋባው ክፍል በዝቶ ፌስታሉ "ሙሽሽ" ብሎ፣ ነበረ የተገኘው።

 የዛን እለት ዶርማችን ብቻ ሳይሆን፣ ኮሪደሩ ብቻ ሳይሆን ላሳሌ ግቢ ሲታመስ ዋለ። ጉልበት፣ ሀይል የመጠቀምና ጉዳት የማድረስ ሀሳቦች ቢነሱም ሀሳቦቹን በሀሳብ መርታት ተችሏል። በመጨረሻ የሀይሉ አቋም "እከሳለሁ ሆነ" ። በህግ ለመዳኘት ክሱ ከሀውስ ፋዘር መጀመር አለበት።

 የተባረረ ተማሪ ዩንቨርስቲው ውስጥ መቆየትም ሆነ መገልገል አይችልም፣ አይፈቀድለትም። የሀይሉ ተስፋዬ በሶ/ጭኮ/ "ተከሳሽ ማነው?" የተባረረ ተማሪ።

 ዩንቨርስቲው ጠንካራ ቅጣት ሊያስተላልፍበት እንደሚችል ብዙዎች አስተያየት ቢሰጡም ሀይሉ ሊመለስ አልቻለም።

ወደ አመሻሽ ላይ የሁለተኛ አመት ተማሪ ሆኖ ከእኛ ከፍረሾች ጋር ዶርም 123 የሚኖረውና በጣም የምናከብረው 'ጌቴ' ጉዳዩን ነገርነው፣

 ጌቴ አነጋገር፣ አቀራረብ፣አገላለጽ ያውቅበታል። ጌቴ በንግግሩ አንስቶ ያፈረጠው ሰው የሚደረሰበት ጉዳት በማንኛውም ወጌሻ ታክሞ የሚድን አይደለም። በሶ/ ጭኮውን ሰርቆ የበላውን ልጅ ጌቴ የገለጸበት መንገድ እዚህ የሚጻፍ አይደለም፣ ለሀይሉ ግን ልጁ ተከስሶ ከሚፈረድበት ቅጣት የበለጠ እርካታ አላብሶት የክስ ሀሳቡን ከጭንቅላቱ ፍቆ አጠፋው።

********

Previous
Previous

የዘመኑ ሳይንቲስትና ምርጥ ሰው (ዶ/ር ተወልደ)

Next
Next

የሰሌ ስናኮች