የሰሌ ስናኮች

ለማስታወስና ለመተዋወስ.....

ዩንቨርስቲ ይዘን የምንወስዳቸው የነበሩ እንደ ዳቦ፣ ዳቦ ቆሎ፣ቆሎ፣በሶ የመሳሰሉ ደረቅ ስንቆችና አጠቃቀም የተመለከተ አንድ ትውስታ ላካፍላችሁ አስቤ ተነሳሁ። ነገር ግን በዚያው ዙርያ ሌላ ሀሳብ መጣና "እኔ እቀድማለሁ" ብሎ ገባ፣ ምን ይደረጋል? ይተረካል እንጁ!

አንዳንድ ጉዳዮች ላይ ስም አይጠቀስም፣ነገር ግን ታሪኩን ለማስኬድ "አንድ ስም " መጠቀም አስፈለገኝ። ስለዚህ ሶስት ስሞችን አስቀመጥኩ፣ አዳሙ፣ ሰለሞን እና ጌታቸው። ከሶስቱ ውስጥ "በባህላዊ" መንገድ አንድ ስም በእጣ አወጣሁ፣ "ሰለሞን" የሚለው ስም ወጣ፣ ስለዚህ ይህንን ባለታሪክ "ሰለሞን" በማለት አቀርባለሁ።

በ1980 ዓ.ም ዶርማችን ውስጥ ከማንም ጋር የማይተዋወቅ አንድ ልጅ መጣ። ክፍሉን በአይኑ ቃኘ፣ ከእኔ አልጋ በላይ ክፍት መሆኑን አይቶ "እኔ ይዤዋለሁ!"ብሎ ሄደ።

ሰለሞን ይባላል። ከሰለሞን ጋር ለአንድ አመት አንድ ዶርም አብረን ኖረናል ። እኔ ሶስተኛ አመት ነበርኩ፣ እሱ ሁለተኛ አመት።

ክፍሉን አይቶና አልጋውን መርጦ የወጣው ሰለሞን ብዙም ሳይቆይ የተማሪ ሳይሆን " ቤት የቀየረ የአንድ ቤተሰብ እቃ " ይዞ መጥቶ ገባ።

ከሀውስ ፋዘር አንድን ቁም ሳጥን አስፈቅዶ ይዞ አመጣ፣ በፊት በዶርሙ ከነበሩት በተጨማሪነት አንድ ጠረጴዛና ወምበርም ተሰጠው።

የሰሌ ቁም ሳጥን ሁለት ክፍሎች አንደኛው ለአልባሳት ሲሆን ሁለተኛው ክፍል በተለያዩ ምግቦች እና የምግብ /መመገቢያ ቁሶች የተሞላ ነው።

ከምግቦቹ ውስጥ የተለመዱት ቆሎ፣ዳቦ ቆሎ እና በሶ አሉ። ቆሎው አይነት አለው፤ ኖርማል ቆሎ ፣ ያልተፈተገ ቆሎ እና በማር የታሸ ቆሎ።

ማር፣ ማርማላታ፣ የዳቦ ቅቤ።

በግቢያችን የሚቀርበው ምግብ ፍራፍሪ የማያሟላ መሆኑን በመጥቀስ የተሟላ ለማድረግ ያልተፈተገ የገብስ ቆሎ በተጨማሪ ሰሌ ብርቱካን እና ሙዝ ገዝቶ ይጠቀማል፣ ዶርማችንም በብርቱካን መአዛ ይታወዳል።

ሰሌ የተሟላ የሚባል የመመገቢያ ቁሳቁሶች አሉት። ለምሳሌ የተለያየ መጠን ያላቸው ዝርግ ሰሀኖች። የቆሎ ማቅረቢያው ሰሐን ዳቦ አይቀርብበትም። የማርና ማርማላታ መቀቢያና የዳቦ መሰንጠቂያ ቢላዋ ብርቱካን አይቆረጥበትም። በሶ በፍጹም በበጠበጠበት ፕላስቲክ አይጠጣም፣ የበሶ መጠጫ ኩባያዎች አሉት።

የሰሌ የዶርም ውስጥ አበላል የራሱ ስርአት አለው። ከሚቆረጠሙት በስተቀር ሌሎች ምግቦቹን ልክ እንደ ምግብ ቤት ጠረጴዛ ላይ ደርድሮ አስቀምጦ ነው የሚመገበው። ለምሳሌ ማታ ዳቦ ይዞ ይገባል፣ የግቢውን ሳይሆን የግዢ። በእለቱ በዳቦ የሚበላው ( የዳቦ ቅቤ ወይም ማርማላታ) መቁረጫ ቢላዋ፣ ...ሰሀኖች አውጥቶ ያዘጋጃል። ከምግቡ በኋላ የሚወስደው የእለቱ ፍራፍሬ በራሱ የማቅረቢያ ሰሀን ከነ የራሱ መቁረጫ ቢላዋ ጠረጴዛው ላይ ከደረደረ በኋላ ነው ተቀምጦ የሚመገበው።

ከምግብ በኋላ እቃዎቹ ተጣጥበውና ደራርቀው ወደ መቀመጫቸው፣ ሰሌ የሚቆረጣጠሙትን ይዞ በአንሶላ የተከበበው "የአልጋ ክፍል "ይገባል።

ሰሌ ስፖርት ያዘወትራል፣ሰውነቱም ጥቅጥቅ ያለ ነው።

የሰሌ ቁምሳጥን ሁለተኛው ክፍል የአልባሳቶች ማኖርያ ነው።ልብሶቹ በስርአት ነው ድርድራቸው፣ ያልታጠቡ ልቦሶቹ እንኳን ተጣጥፈው ነው የሚቀመጡት፣ ከታች የጫማዎች መደርደርያ ነው። የሰሌን አልባሳቶቹን ሳስታውስ ፣ የአመጋገብ ስርአትና የምግብ ቁሳቁሶችን የምግብ ባህሉን ሳስታውስ በቤተሰብ የሚተዳደር የነበረ እና በቀጥታ ከትምህርት ቤት ሳይሆን ከስራ አለም የመጣ ነበር የሚመስሉት።

አይ ሰሌ! የዚያን ጊዜ ተረከዟን አጥፎ እንደ ነጠላ ጫማ የሚጠቀምባት ዘናጭ ሲንተቲክ ጫማ "እረ ይሄ ጫማ እንደዚህ የሚንገላታ አይደለም!" ስለው ከፈለክ ውሰደው ብሎ የሰጠኝን መዘነጫ እንዳደረኳት ሳልጠቅስ ብቀር ጸጸቱ ለእኔው ነው ።

አዲስ ሰውን ልክ እንደ አሁኑ ከስሙ በፊት " ከየትነቱ " ቀድሞ የሚጠየቅበት ጊዜ ባለመሆኑ ሰሌ በወሬው መሀል ጎንደር መሆኑን ብዙ ቆይቼ ነው የተረዳሁት።

ሰሌ ብዙውን ጊዜ ሜይን ካምፖስ ሲያጠና አምሽቶ ነው የሚመጣው።

በተከለለው አልጋው ውስጥ እያጠና የቆሎና የዳቦ ቆሎዎች ቁርጠማ ድምጽ ነው ለዶርሙ ተማሪ የሚያካፍለው ወይም የሚያበረክተው።

ከሰሌ ምግቦች የመቃመስ እድል ያገኘሁት እኔ ብቻ ሳልሆን አልቀርም፣ ከሌሎቹ ሳይሆን ከቆሎና ዳቦቆሎዎቹ።

"ኮርሸም፣ኮርሸም፣ኮርሸም....ትንሽ ቆይቶ ኮርሸም....ኮርሸም.....ኮርሸም ። በዚህ ድምጽ ትንሽ ካዝናናን በኋላ ቀርጨጭ...ቀርጨጭ....ቀርጨጭ...ይተካል።

እሱ ከዶርም ውስጥ እራቱ በኋላ የሌሊቱን ጥናት ሲጀምር እኔ ተኝቻለሁ። ድምጽ እንዳልሰማ ትራስ ጭንቅላቴ ላይ ጭኜ። በአጋጣሚ ካልተኛሁ፣

"አንተ!" ይጠራኛል።

"አቤት" ፣

"እንካ! "

ብሎ በራስጌ በኩል ወደታች እጁን ይዘረጋል። ሰሌ መብላት ብቻ ሳይሆን ሲሰጥም በራሱ ልክ ነው።

********

አንዳንድ ጊዜ የሰሌ "ተጨማሪ አመጋገብ" እሱ በሌለበት ይነሳና ብዙና የተለያዩ አስተያዬቶች ይሰነዘራሉ፣ ይጎርፋሉ፣ በአሉታም- በአወንታም በነቀፊታም ... ።

"መብቱ ነው " በአንድ በኩል ይቀርባል፣።

" የእሱ መብት ሌሎቻችንን ሰላም የሚያደፈርስ መሆን የለበትም!" በሌላው ጥግ ያለው ።

"ይሄ መኝታ ክፍል እና ማንበቢያ እንጂ መመገቢያ አይደለም።......." ከእኔ ጎን ያለው፣

"ጫት ሲቃመበት፣ ሲጋራ ሲጨስበት አይደለምንዴ የሚዋልና የሚታደርበት? ሌላው ..

አንዱ በአንሶላ በተሸፈነ አልጋው ውስጥ ሆኖ የአይጥ ጉዳይ አነሳ።

".... ይሄው በእሱ ምክንያት፣ በእሱ የምግብ ትራፊና የምግብ ሽታ ዶርማችን አይጥ መጣ....."

ብሎ እየተናገረ እያለ ሰለሞን ወደ ዶርም መግባቱን የተመለከቱት ሌሎቹ ዝም ሲሉ የአይጥ ጉዳይ ያነሳው ልጅ ወሬውን ቀጥሏል። የሚስቅለት፣ የሚደግፍም ሆነ የተቃውሞ ምላሽ ያጣውና የሁሉም ጸጥ ማለት ግራ የተጋባው ልጅ የከለለውን አንሶላ ወደ ላይ ብድግ ሲያደርግ ሰለሞንን ዶርሙ መሀል ይመለከተዋል።

የሰለሞን የሰውነት አቋም ከላይ የጠቀስኩት ነው። ዶርሙ ውስጥ አንዳንዴ ጫጫታ ሲበዛ ሰሌ ቁም ሳጥኑን በቡጢ መትቶ በማስጮህ ነው ጸጥታውን የሚመልሰው። ጸጥ እንዳለለትም ከበድ፣ከበድ ያሉ ቃሎችን ይሰነዝራል፣ የሀይል እርምጃ እንደሚወስድ ጭምር።

ሰለሞንን እንዳየው ልጁ እንደሚደነግጥ ጥርጥር የለውም። በድንጋጤ ምን አደረገ?

ልጁ የጀመረውን የአይጥ ጉዳይ ወሬውን ቀጠለ።

" የሚገርማችሁ .....እዚህ ዶርም ብቻ እኮ አይደለም! የሚቀጥለው ዶርም እራሱ ብዙ አይጦች አሉ። የእዚያ ዶርም አይጦች የብዙ ልጆች ጫማችንን በልተውብናል ሲሉ ሰምቻለሁ። ልጁ አሁንም ቀጠለ፣ "ለሀውስ ፋዘር ማሳወቅ አይሻልም....

..ሌላም፣ ሌላም።

Previous
Previous

የሀይሉ በሶ

Next
Next

ዶ/ር ጌታቸው ቦሎድያ በአስመራ