የዘመኑ ሳይንቲስትና ምርጥ ሰው (ዶ/ር ተወልደ)

አዲሱ

 ዶ/ር ተወልደን ለመጀመሪያ ጊዜ ያየኋቸው በ1975 ኢ/ር ተከስተን ተክተው ሲመጡ በትልቁ ህንጻ መሀል (Courtyard) በተካሄደ የምሽት ዝግጅት ላይ ይመስለኛል፡፡ ከዚያ በኋላ ካምፓስ ውስጥ ከባለቤታቸውና ከልጆቻቸው ጋር አንዳንዴ አያቸው ነበር፡፡ ሙሉ የጎልማሳ ሰውነት፣ መካከለኛ ቁመና፣ ደማቅ ቅላት፣ ጥቅጥቅ ያለ ጸጉር፣ ክብ ቅርጽ ያለው ጥቁር ጺም… እንደነበራቸው ትዝ ይለኛል፡፡ በመጨረሻ ደግሞ በምረቃችን ዕለት ባደረጉት ድንቅ ንግግር አስታውሳቸዋለሁ፡፡ በዩኒቨርሲቲ ቆይታዬ ስለሳቸው የነበሩኝ ትውስታዎች እነዚሁ ነበሩ፡፡

ወደ ስራ ዓለም ከተሰማራን ከዓመታት በኋላ በ80ዎቹ አጋማሽ ላይ ቦሌ መንገድ ፍላሚንጎ በሚገኘው የተፈጥሮ ሀ/ልማትና የአ/ጥበቃ ሚኒስቴር ዶ/ር ተወልደን እንደገና አየሁዋቸው፡፡ ካምፓስ ከማውቃቸው ትንሽ ተለውጠዋል፡፡ ቅላትና ወዘናቸው በመጠኑ ወይቧል፣ ጸጉርና ጺማቸው ላይ ሽበቶች ተፈነጣጥቀዋል፣ ከትከሻቸው ትንሽ ሰግደድ ያሉ ይመስላሉ፡፡ በዚያን ጊዜ የ National Conservation Strategy Director ነበሩ፡፡ ፕሮጀክቱ ከማዕከላዊ ፕላን ወደኛ ሚ/ር ሲካተት ነው የመጡት፡፡ የቅርብ አለቃዬ ከነበረው (ም/ሚ/ር በኋላ ሚኒስትር) ፕሮፌሰር መስፍን አበበ ጋር በስራ ስለሚገናኙና ወዳጅም ስለሆኑ በየጊዜው አገኛቸው ነበር፡፡ የነበራቸው የስራ ፍቅርና ጥንካሬ አስገራሚ ነበር፡፡ ስራቸው ህይወታቸው ሆኗል፡፡ በኋላ ላይ ልጆቻቸው ቢሯችን ሲመጡ እንዳየሁት፤ አ.ዩ. ግቢ ውስጥ የኤለመንታሪ ዩኒፎርም ለብሰው፣ ነጭ ካልሲ አጥልቀው ጡብ ጡብ ሲሉ የነበሩት ህጻናት ልጆቻቸው እነ ሮሚ በጣም አድገው የኛ እኩያዎች መስለዋል፡፡ 10 ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የታዩት ለውጦች ያስገርማሉ፡፡ በዶ/ር ተወልደ ላይ ለተከሰተው አካላዊ ለውጥ፤ የነበረባቸው አለርጂ፣ የደረሰባቸው የመኪና አደጋና በጥይት የቆሰሉበት አጋጣሚ የየራሳቸውን ተጽዕኖ አሳርፈዋል፡፡ (Btw በወቅቱ ያከሟቸውና ጥይቱን ያወጡላቸው ፕሮፌሰር አስራት ነበሩ)

In 1986, after Rio Earth Summit, Ethiopian Environmental Protection Authority was etstablished. በዘርፉ ልምድ የነበራቸውና የሀርቫርድ ምሩቅ የሆኑት ዶ/ር ዘውዴ አባተ በኃላፊነት ተሾሙ፡፡ እኔም በመ/ቤቱ ውስጥ ተመደብኩ፡፡ በማደራጀት ተግባር ላይ እያለን፤ ዶ/ር ዘውዴ አሜሪካን አገር ለህክምና ሄደው አረፉ፡፡ በ1987 ዶ/ር ተወልደ የባለስልጣኑ ዋ/ስ/አስኪያጅ (ዳይሬክተር ጀነራል) ሆነው መጡ፡፡ የቅርብ አለቃዬ ሆኑ፡፡ የስራው ባህርይ በየቀኑ ስለሚያገናኘን፣ ወደ ውጪ ሲሄዱም በአብዛኛው እኔን ስለሚወክሉ፣ ፋታ በማይሰጥ የስራ ዑደት ውስጥ ሲሆኑ ከኔ የስራ ድርሻ ጋር በቀጥታ ለማይያዙ ጉዳዮችም እኔን ማዘዙ ስለሚቀላቸው… እሳቸውን በቅርበት ለማወቅ ዕድሉ ነበረኝ…

ዶ/ር ተወልደ ያረፉት መጋቢት 12/2015 ነው፡፡ ዛሬ 2ኛ ሙት ዓመታቸው ነው፡፡ ስለዚህ ስለሳቸው ከተጻፉት ውስጥ ለየት ያሉትን፣ ብዙም ያልተወሱትንና በግለ-ታሪካቸው ያልተዳሰሱ አንዳንድ ነጥቦችን እያነሳን ሰሞኑን እንዘክራቸዋለን!

 -----

ሚዶራ

 ቆንጆ ትውስታ ነው። በርግጥ ካልተሳሳትኩ ዶ/ር ተወልደ ለመጀመሪያ ለዩኒቨርሲቲው ማ/ሰብ ንግግር በማድረግ እራሳቸውን በኦፊሴል ያስተዋወቁት በ1976 ዓ/ም በዩኒቨርሲቲው ልማድ መሰረት በተለይም በየአመቱ ለሚመጡት አዲስ ገቢ ተማሪዎች 'The president's annual speech delivery addressing the university community' ወይም በተለምዶ ፍሬሽ ፓርቲ በሚዘጋጅበት ዕለት ይመስለኛል። ምናልባት ኢ/ር ተከስተ አኽደሮም የ 1975 ን የትምህርት ዘመን በነበራቸው ሀላፊነት ሳያጠናቅቁ ወደ የከተሞች ልማት ጥናት ኢንስቲትዩት ዳይሬክተርነት (ስሙን በትክክል ጠርቼው ከሆነ) ተሹመው በመሄዳቸው በዶ/ር ተተክተው ከነበረ ዓ/ምህረቱ 1975 ሊሆን ይችላል....

በዚህ ዕለት ከማይረሱኝ ነገሮች አንደኛው በቋንቋና ስነ ፅሁፍ ትምህርት ክፍል መምህር የነበሩት ህንዳዊው ዶ/ር ራኦ እና በማኔጅመንት ዲፓርትመንት መምህር የነበሩት ሚስስ ራኦ ብቸኛ ሴት ልጅ የህንድን ባህላዊ ውዝዋዜ/ዳንስ እያሳየች ለተማሪዎች ከታደለው ለስላሳ አንዲት የጠርሙስ ክዳን ቆርኪ (ማንም ባላየበትና ወይም ትኩረት ባልሰጠበት) በውዝዋዜው ሜዳ ላይ ወድቃ የተመለከቱት ዶ/ር ተወልደ ልጅቷን ያደንቅፋታል/ይጥላታል በሚል ባልተጠበቀ ሁኔታ በክብር እንግድነት ከተቀመጡበት ብድግ ብለው ሌሎችን ላለመረበሽ ጭንቅላታቸው ዝቅና በጣም አጎንብሰው በሩጫ ቆርኪዋን አንስተው በሩጫ ወደ መቀመጫው የተመለሱበትና የዩኒቨርሲቲው ማ/ሰብ በሳቅና በሁካታ ክስተቱን ያጀበበት ገጠመኝ ነው። ከራስ ክብርና ምቾት ይልቅ ምን ያህል ለሌሎች የሚሰጡትን ግምት እንዲሁም ላቅ ያለ እራስን ዝቅ አድርጎ ትህትናን የማሳየት ስብዕናን የሚያመለክት አስተማሪ ተግባር ነው!

ቅዱስ መፅሀፉም እራሱን ዝቅ ያደረገ ከፍ ይላል ይልም የለ...በትክክልም ዶ/ር ተወልደ ዝክርም ክብርም ይገባቸዋል።

-------

ሙሴ

@⁨~ADDISU MEKONNEN⁩ ዶ/ር ተወልደብርሃንን አስተውሰህ እንድናስታውሳቸው ስላደረግክ ከልብ እናመሰግንሀለን::

መተዋወስ ስላልቻልን እንጅ እ.አ.አ 1999 ወይም 2000 አካባቢ (ወሩን በውል አላስታውሰውም) እኔም በመስሪያቤታችሁ የስብሰባ አዳራሽ በተደረገ ስብሰባ ተገኝቼ ነበር:: እጅግ ብዙ ተሳታፊ እንደነበር ትዝ ይለኛል::  

ባልሳሳት ያንጊዜ ትልቁ ውይይት መለ-ዘራቸው ስለተለወጠ ሥነፍጥረታት (Genetically Modified Organisms) ነበረ:: ለማህበራዊ ሳይንስ በተለይም ለኢኮኖሚክስ ተማሪዎች ሳይንሱ ሳይሆን ወደ ጉዳዩ ያስገባን GMOs በዓለምአቀፍ ምርትና የንግድ ሥርአት ላይ በሚኖራቸው በጎም ይሁን አሉታዊ ተፅእኖዎች በሚመለከት ነበር:: ይህ ጉዳይ በዓለምአቀፍ ንግድ ስምምነቶች ላይ የሚኖረው ተፅእኖ ሰፊ ውይይትና ክርክር የሚደረግበት ወቅት ነበር:: በጊዜው የነበረው ሰፊ የአመለካከት ልዩነት በበለፀጉና ገና በመልማት ላይ ባሉ ሀገሮች መካከል ብቻ ሳይሆን በበለፀጉ ሀገሮች መካከልም ጭምር ብርቱ ክፍፍል የፈጠረ ጉዳይ ነበር::

 ወደ ዶክተር ተወልደብርሃን ልመለስና በወቅቱ ኢትዮጵያ የWTO አባል ባትሆንም (ዛሬም አይደለችም) እሳቸው በማደግ ላይ ያሉ ሀገሮችን ( በተለምዶ ቡድን 77 በሚባለው) ውስጥ ከፍተኛ ሚና እንደነበራቸው ይታወቃል:: ነገር ግን WTO ውስጥ ለመሳተፍ የሀገር ውክልና ስለሚያስፈልግ ተወክለው የመጡት በኢትዮጵያ መንግስት ነበር:: ኢትዮጵያ ደግሞ ያኔም ይሁን አሁን ያላት እድል በድርጅቱ ስብሰባዎች ላይ መሳተፍ የምትችለው በታዛቢነት ብቻ ነበር:: ይህ ማለት መታዘብ የምትችለው "public meetings" የሚባሉትን እንጅ እውነተኛ ክትክት የሚደረግባቸውን ድርድሮች መካፈል አትችልም ነበር:: ክትክት ያልኩት በምክንያት ነው:: እጅግ ውስብስብና አንዳንዴም ግልፅ መገፋፋቶች የሚስተናገዱበት ስለነበር ነው::

 በዚያን ጊዜ በተለይም ("Green House") ውስጥ በመባል በሚታወቁ የስብሰባ አዳራሾች የሚደረጉ ድርድሮችን አለመካፈል ማለት ምንም አይነት ተፅእኖ አለማድረግ ማለት ብቻ ሳይሆን ያልተሳተፉበት ምስጢራዊ ስብሰባዎች ላይ የተላለፉ ውሳኔዎችንም መቀበል ማለት ነው::

አሁንም የWTO ትላልቅ ጉዳዮችና ውይይቶች የሚጠናቀቁት በአረንጓዴ ቤቶች በሚደረጉ ምስጢራዊ ድርድሮች ላይ በሚደረሱ ስምምነቶች ነው:: በዚህ ምክንያት ነው ድርጅቱ ሀያላን ሀገሮች የንግድና ልማት ፍላጎቶቻቸውን በድሀ ሀገሮች ላይ እንዲጭኑ የሚያመቻች ነው ተብሎ በሰፊው የሚተቸው::

ለማንኛውም በዚህ ምክንያት ዶር ተወልደ በአስፈላጊ ውይይቶች ላይ እንዳይከፈሉ ስለተደረጉ ዘዴ ተፈለገና በቡድን 77 አማካኝነት ስብሰባ ውስጥ እንዲገቡ ስምምነት ላይ ተደረሰ:: ነገር ግን እጀ-ረጅሙዋ ሀገር (የትኛዋ እንደሆነች ይታዎቃል ብዬ ነው...😂) ይህንን ጥንስስ ደረሰችበትና ለሰክረታሪያቱ ጥብቅ ትእዛዝ ተላለፈ:: ይህም "የድርጅቱ አባል ያልሆኑ ሀገሮች ተወካዮች በፍፅም "Green House" ውስጥ እንዳይገቡ" የሚል ነበር:: በዚህ ምክንያት ዶ/ር ተወልደ በቡድን 77 ስምም ጭምር እንዳይገቡ ተደረገ::

በመቀጠል የነበረው አማራጭ ዶ/ር ተወልደ ከቡድን 77 ተደራዳሪዎች ጋር በቅድሚያ እንዲወያዩና በዚህም በቡድኑ ውስጥ አንድ ወጥ አቁዋም እንዲያዝ ሌላ መንገድ ተቀየሰ:: ማታ ለሚካሄድ የድብቅ ድርድር ቡድን 77 ከሰአት በሁዋላ 3pm ላይ እንዲሰበሰብ ተወስኖ ይሄው በምሳ ሰአት ላይ announce ተደረገ:: "በዚህ ሰአት በዚህ room ውስጥ የቡድን 77 ስብሰባ ይደረጋል" ተባለ:: ልክ ለስብሰባው 15 ደቂቃ ሲቀር ይህም ስብሰባ ተሰረዞአል ተብሎ የውስጥ መልእክት ተላለፈ:: "ማነው ስብሰባውን ያሰረዘው" ሲባል አሁንም እጀ ረጅሙዋ ሀገር "አባል ያልሆኑ ሀገሮች በድርጅቱ የስብሰባ አዳራሾች ውይይት መምራት አይችሉም" በሚል ነበር::

ምንም ማድረግ ስላልተቻለ ዶ/ር ተወልደብርሀን ያዘጋጁት ከአምስት ገፅ ያልበለጠ የአቁዋም መግለጫ ለሁሉም ቡድን 77 አገሮች በemailና በፋክስ በሚሲዮኖቻቸው አማካኝነት እንዲደርሳቸው ተደርጎ የእለቱ የማታ የድብቅ ስብሰባ ያለውጤት እንዲበተን ምክንያት ሆነ:: ዝግጅት የሚደረገው ኖቬምበር 1999 ውስጥ በ Seattle Washington State ለሚካሄደው የWTO Ministerial Conference ነበር::

ታዲያ በዶ/ር ተወልደብርሀን በተዘጋጀ ረቂቅ ሰነድ ላይ አንዳንድ ግልፅ ያልሆኑና መብራራት ያለባቸው ጉዳዮች ስለነበሩ ስብሰባ እንደሚያስፈልግ በተደረሰ ስምምነት UNCTAD እንዲያመቻች በመጠየቁ ስብሰባው WTO ውስጥ መደረጉ ቀርቶ በUNCTAD የስብሰባ አዳራሽ እንዲደረግ ሆነ::

በዚህ ስብሰባ ላይ ዶ/ር ተወልደ GMOs በአካባቢ ላይ በተለይም በእንስሳት በእፅዋት በአፈር በውሀና በሌሎችም ህይወት-አቀፍ በሁኑ ጉዳዮች ላይ ሊኖራቸው ስለሚችል ተፅእኖ በዝርዝርና በማስረጃ አስጨበጡ:: ስብሰባ tense የሚሉት አይነት ነገር ነበር:: ሀሳብም ጭንቀትም የሞላበት አይነት ነገር:: "ዛሬ የምናሳልፈው ውሳኔና የምንፈርመው ስምምነት 4 እግር ያለው ቀለሙ የተለወጠ (አረንጉዋዴ, ቢጫ) ሰው ወይንም በአንድነት የተጣበቁ እንስሳት; ጥርሳ ያላቸውና መርዛማ የሆኑ አእዋፍ; ሁለት ወይም አራት እግር ያላቸው ዘንዶ/እባቦች; ፍሬ የማያፈሩና የማያብቡ ተክሎች; በአንድ ቀን ፍጡርን ከምድረ-ገፅ የሚያጠፉ ጀርሞችና ባክቴሪያዎች ወዘተ መቀበላችሁን አረጋግጡ" የሚል ልመናም ጭምር የነበረበት ማጠቃለያ ነበር ዶ/ር ተወልደ የሰጡት::

 ከዚህ በሁዋላ የሆነው የሚገርምና የሚያስቅም ነበር:: የኢራን ተወካይ አስር ደቂቃ የወሰደ ንግግር ፀሎትና እርግማን እንዲሁም የቫቲካን ተወካይ ያደረጉት ረዥም ፀሎት እድሜ ልኬን የማይረሱኝ ናቸው:: ሁሉም በንግግራቸውና በፀሎታቸው ያስተላለፉት ይህንን የተፈጥሮ ጠንቅ የፈጠረች ሀገር (እጀ ረዥሙዋን ማለታቸው ነው) ወይ አሳቢ አእምሮ ይስጣት ካልሆነም ከምድር ላይ ያጥፋት የሚል ተማፅኖ ነበር::😂😂😂

ሲጠቃለል የ WTO የሲያትል የሚኒስትሮች ስብሰባ ያለምንም ስምምነት እንዲጠናቀቅ የ GMOs ጉዳይ አንዱና ዋናው ምክንያት ሲሆን ዶር ተወልደብርሃን የቡድን 77 ልዑካኖችን በማንቃት ያደረጉት ጉልህ አስተዋፅኦ ሲዘከር ይኖራል:: እኛ ባንዘክራቸው ይህንን ዓለምአቅፍ ህብረተሰብ በተለይም ቡድን 77 ይዞት እንደሚጉዋዝ ጥርጥር የለኝም!!

በዚሁ ይብቃኝ.....

 ----

አዲሱ

Hi Mussie, Thank you so much. Very insightful and informative. 🙏🏼🙏🏼

እውነት ነው፤ ዶ/ር ተወልደ በዕውቀት የተደገፈ ጠንካራ የንግግርና የማሳመን ችሎታ ስላላቸው የብዙዎችን አስተሳሰብና የዓለም አቀፍ ድርድሮችን አቅጣጫ ማስለወጥ እንደሚችሉና፣ በውይይት ሊቋቋሟቸው እንደማይችሉ ሲገነዘቡ ምዕራባውያኑ፣ አንተ በሚገባ እንደገለጽከው ተሳትፏቸውን ለመገደብ የተለያዩ ተጽዕኖዎችን ያደርጉባቸው ነበር፡፡ በካናዳ የ Bio safety (Liability and redress) ወሳኝ ስብሰባ/ድርድር ሲካሄድ እሳቸው እንዳይሳተፉ ቪዛ እስከ መከልከል ደርሰው ነበር፡፡ጉዳዩ ዓለም አቀፍ ዜና እና መነጋገሪያ ሆኖ፤ የካናዳ ምክር ቤትና ጠቅላይ ሚኒስትር ዘንድ ደርሶ ከአቅም በላይ የሆነውን ዓለም አቀፍ ተቃውሞ በመፍራት ቪዛ እንዲሰጣቸው ተደርጎ 2 ቀን ዘግይተው በስብባው ላይ ተሳትፈዋል፡፡

-ተወልደ ዘመናዊ ትምህርት የጀመሩት በ11 ዓመታቸው ነው፡፡ እስከ 8ኛ ክፍል ያለውን ትምህርት ያጠናቀቁት ግን በ4 ዓመት ውስጥ ነው፤ ‘Double’ ብቻ ሳይሆን ‘Triple’ ተዛውረው ነበር፡፡ የሚኒስትሪ ውጤታቸው በአገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ነጥብ ካገኙት ውስጥ ነበር፡፡

-ከጀነራል ዊንጌት የ2ኛ ደረጃ ት/ታቸውን በከፍተኛ ውጤት አጠናቀው ወደ አ.አ.ዩኒቨርሲቲ ሲገቡ ያለመጫሚያ በባዶ እግራቸው ነበሩ፤ ተመርቀው ሲወጡ ግን የወርቅ ሜዳሊያ አጥልቀው ነበር፡፡

-በዩኒቨርሲቲ የ3ኛ ዓመት ተማሪ እያሉ ህክምና ለማጥናት ወስነው ዕድሉንም አግኝተው ነበር፡፡ ሀሳባቸውን ቀይረው በጀመሩት የስነ ህይወት ትምህርት ጨረሱ፡፡

-አ.አ.ዩ. ት/ት ያጠናቀቁበት GPA ለተወሰኑ ዓመታት የፋካልቲው ሪኮርድ ሆኖ ቆይቷል፡፡

-ዶ/ር ተወልደ የማስተርስ ዲግሪ የላቸውም፤

-ከባችለር ዲግሪ በቀጥታ PhD ሰርተዋል፡፡ የUK የት/ት ስርዓት በጣም ከፍተኛ ውጤት ያላቸው በቀጥታ PhD እንዲሰሩ ስለሚፈቅድ ነው፡፡

-PhD የሰሩት University of North Wales ነው፡፡ የሚገርመው ነገር፤ ለትምህርት ወደ ውጪ ሲሄዱ ከአ.አ. ዌልስ የደረሱት አይሮፕላን ሳይሳፈሩ ነው፡፡ አገር እያዩ ለመሄድ ፈለጉ፡፡ ‘ልጅ ነህ በመንገድ ችግር ሊያጋጥምህ ይችላል…’ ቢባሉም፤ ስኮላርሺፕ የሰጣቸውን የቀዳማዊ ኃ/ስላሴ የሽልማት ድርጅት፣ እንደምንም አሳምነው የአየር ትኬቱን ገንዘብ ተቀበሉ፡፡ ብራቸውን በትራቭለር ቼክ ይዘው በአውቶቡስ፣ በባቡር፣ በጀልባና በመርከብ እያቆራረጡ... በአስመራ፣ በተሰነይ፣ በከሰላ፣ በካርቱም፣ በካይሮ፣ በደማስቆ፣ በኢስታንቡል፣ በግሪክ፣ በዩጎዝላቪያ፣ በጣሊያን፣ በፓሪስ፣ በሎንዶን፣ አድርገው፣ ከ1 ወር በላይ ተጉዘው ዌልስ ደረሱ፡፡ አስቡት፤ ገና የ24 ዓመት ወጣት ነበሩ…

-ዶክተር ተወልደ፣ እንደ ፍጡር ፍጹም ስላልሆኑ፣ የተሳሳተ ውሳኔ ሊያስተላልፉ ይችሉ ይሆናል፡፡ ሆኖም ውሳኔያቸውና አጠቃላይ አመለካከታቸው፤ በትውውቅ፣ በወዳጅነት፣ በጥቅም፣ በዝምድና፣ በአገር ልጅነት… በፍጹም-በፍጹም የሚዛነፍ አይደለም፡፡ ለህሊናቸው፣ለሀቅ፣ ለዕውነት፣ ለፍትህ፣ የማይናወጽ አቋም አላቸው፡፡ እያጋነንኩ አይደለም፤ ከአድሎ የጸዱ ሰው ናቸው፡፡ በአገር ውስጥ ያለው ጎሰኝነት፤ በጥቁር፣ በነጭና በቢጫ ህዝቦች መካካል ያለው ልዩነት ብዙም ሳይጫናቸው፤ ሰውን በሰውነቱ ወደሚመዝኑበት ላቅ ያለ የሞራል ልዕልና ደርሰው ነበር፡፡

-የሀብት ፍላጎት አልነበራቸውም፡፡ በአንድ ወቅት ሙሴ እዚህ ገጽ ላይ እንዳሰፈረው፤ በማናቸውም ሁኔታ የተለየ መስተንግዶ ወይም የተለየ ጥቅም ለማግኘት አይሹም፡፡ ከደመወዝ በተጨማሪ የውጭ ጉዞ ሲያደርጉ አበል ያገኛሉ፡፡ ምንም ሱስ የለባቸውም፡፡ ተጨማሪ ገንዘብ ሲያገኙ ሌላ ችግረኛ ልጅ ስለመርዳት እንጂ ስለንብረት አያስቡም፡፡ መኖሪያ ቤታቸው በተደጋጋሚ ሄጃለሁ፡፡ ከመሰረታዊ መገልገያዎች ውጪ የቅንጦት ዕቃ አይታይም፡፡ በስተመጨረሻ አስኮ ቤት እስኪሰሩ ድረስ ለረጅም ዓመታት በፈረንሳይ፣ በኦልድ ኤርፖርትና በዘነበወርቅ፤ በኪራይ ቤት ኖረዋል፡፡ የመኖሪያ ቤት ከመንግስት መጠየቅ ወይም ለኪቤአድ ትዕዛዝ ማሰጠት ቢችሉም አያደርጉትም፡፡ ወደ ዘነበወርቅ ሲቀይሩ አብሬያቸው ነበርኩ፡፡ አ.አ. ኪቤአድ ጽ/ቤት እና ጆስ ሀንሰን አካባቢ ወደሚገኝ የቀጠና 2 ጽ/ቤት አብረን ተመላልሰናል፡፡ እንደማንኛውም ዜጋ ማመልከቻ አቅርበው፣ ፋይላቸውን ከመዝገብ ቤት እያስፈለግን እንከታተል ነበር፡፡ ጥያቄያቸው ቀላልና ግልጽ ነበር፤ ብዙ ልጅ የሚያሳድጉበት ሰፋ ያለ ቤትና አንዳንድ የዕጽዋት ምርምር የሚያካሂዱበት መጠነኛ ጓሮ ብቻ…

-ከባለቤታቸው ከወ/ሮ ሱ (ዕህተ ብርሃን) ጋር 60 የሚሆኑ ልጆችን አሳድገዋል፡፡ ስላሳደጓቸው ልጆች ብዛት በጋዜጠኛ ሲጠየቁ፣ ምላሻቸው ‘ምን ሊያደርግልኝ እቆጥራቸዋለሁ…?’ የሚል ነበር፡፡ መለከት አይወዱም፡፡ ያሳደጓቸው ልጆች ከተለያየ አካባቢ የመጡ ሲሆን፤ በአመጋገብ፣ በአልባሳትና በወላጅ እንክብካቤ ረገድ በስጋ ከተወለዱት ልጆች ጋር ተመሳሳይ መብት ነበራቸው፡፡ ይህን በቅርበት አይቻለሁ፡፡ በቤታቸው ከሚያሳድጓቸው ልጆች በተጨማሪ በየወሩ መ/ቤታችን መጥተው ለልጆቻቸው መጠነኛ የገንዘብ ድጋፍ የሚወስዱ እናቶችም ነበሩ፡፡

-----

ሙሉጌታ

ዶር ተወልደ ብርሃን ፣ ደርግ ሊወድቅ አካባቢ ፣ አለማያ ዩኒቨርሲት በተጋባዥነት መጥተው ነበር። ሀረር ከተማ የሚገኘው ራስ ሆቴል አርፈው ወደ ማታ በእግራቸው እየዞሩ ሳሉ አገኘኋቸው። የአስመራ ዩኒቨርሲቲ፣ ተመራቂ መሆኔን ስነግራቸው፣ እንዴት፣ እንደ ረጅም ጊዜ ወዳጅ አቅፈው ፣ እየወዘወዙ እንደሳሙኝ አልረሳውም። ልጆቼን በሁሉም ቦታ ሳገኛቸው የምደሰተው ደስታ መጠኑን መናገር አልችልም ነበር ያሉት። በጨዋታቸው መካከል እንዲህ አሉ። እኔ አሁን ያለሁበት ሁኔታ መልካም አይደለም። ደርግ ፣ ወያኔን ትደግፋለህ ይሉኛል። ወያኔና የአካባቢዬ ሰዎች ደግሞ፣ የደርግ አገልጋይ ፣ ይሉኛል። የገና ዶቦ ሆኛለሁ። አንተን ሳገኝ ሁሉንም ነገር ረሳሁ ታደስኩ። እዚህ ከተማ የማውቀው ሰው አገኛለሁ ብዬ አላሰብኩም ነበር ብለው እያጫወቱኝ እስከ ሆቴላቸው አብረን ተጓዝን። ሳምንት ያክል እንደሚቆዩ ነግረውኝ፣ የመኝታ ቁጥራቸውን ነግረውኝ ተለያየን። በተለያየ ምክኒያት ተመልሼ ባላገኛቸውም፣ እርጋታቸውና፤ አባታዊ ፍቅራቸው የልብ ምግብ ሆኖኛል።

ልብን የሚመረምር እግዚአብሄር ነፍሳቸውን በአፀደ ገነት ያኑርልን።

-----

አዲሱ

ለዛሬ አንድ የመጨረሻ፤ ቀሪዎቹን ለቀጣይ ቀናት…

ተወልደ በጣም ቁም ነገረኛ፣ የተግባርና የመርህ ሰው የመሆናቸውን ያህል፤ ጨዋታ አዋቂም ናቸው፡፡ ሲጫወቱ ለዛ አላቸው፡፡ ከአሁናዊ ኩነቶችና ከቁም ነገር ጋር አዋድደው ዘና የሚያደርጉ የድንገቴ ቀልዶችን፣ ተረትና ምሳሌዎችን በሚጥም መንገድ ማቅረብ ይችሉበታል፡፡ አንዳንዴ ፕራንክ መሰል ነገሮችንም ይሞክራሉ፡፡ በራሳቸው ላይ ለመቀለድም ነጻ ናቸው፡፡ በአንድ ወቅት መስክ ወጥተን ሳለ የአፍሪቃ ይሁን የዓለም ዋንጫ ይካሄድ ነበር፡፡ ያረፍንበት ሆቴል ኳስ እየታየ ስለነበር ስለኳስ ይወራ ጀመር፡፡ እሳቸውም በልጅነታቸው ከኳስና ከስፖርት ጋር ስላላቸው ግንኙነት የሚያስቁ ገጠመኞቻቸውን ነገሩን፡፡ በወቅቱ ከነገሩንና በኋላም ግለ-ታሪካቸው ላይ በከፊል ካሰፈሩት፤ በራሳቸው አንደበት…..

“…ልጆች በነበርን ጊዜ የምንጫወታቸው በርካታ ጨዋታዎች እንደነበሩን አስታውሳለሁ፡፡ እኔ ግን ህመምተኛ ስለነበርኩ ይህንን ያህል በስፋት ተሳታፊ አልነበርኩም፡፡ …በግሌ አንድም ጨዋታ ላይ አሪፍ ነኝ የምለው የለም፡፡ ገበጣ ጨዋታን እወድ ነበር፡፡ ሌላው ላይ ይህንን ያህል ፍላጎት የለኝም፡፡ …. አንዳንዴ ነሸጥ አድርጎኝ በእግር ኳስ ጨዋታ ላይ እሳተፋለሁ፡፡ ኳሷ ተንከባላ ወደ እኔ ስትመጣ ዓይቻት ልለጋት ስሞክር እስትና ሜዳውን እጨረግደዋለሁ፡፡ …ዩኒቨርሲቲ ተማሪ እያለሁ መምህራኖቼ የነበሩት ካናዳውያን ጀዝዊቶች፤ … እኛ እንከፍልልሀለን ብለው፤ አሥመራ ተልኬ የዓይን ህክምና አግኝቼ አይኖቼ ተስተካካሉ፡፡ በኋላ አልሞከርኩም እንጂ ብሞክር ኳስ ብለጋ የምስት አይመስለኝም”😂

ተቀጽላ ……

• በ1983 ለ1 ወር ያህል የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሆነው ተሹመው እንደነበር ይታወሳል፡፡

• በ2000 ደግሞ፣ ባይሰሩበትም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የአማካሪ ቦርድ አባል ሆነው ሳያውቁት ተመርጠው ነበር፡፡

——

ሙሴ

ስለዶር ተወልደብርሃን አውርቶ መጨረስ አይቻልም:: ቀደም ብዬ እንደጠቀስኩት ከዩኒቨርስቲ ህይወቴ ባሻገር ከአአ እስከ ጄኔቫ ከዚያም ከሪዮ ደ ጃኔሮ እስከ ሲያትል (ዋንሽግተን ስቴት) በአካል አግኝቼያቸዋለሁ (ተገናኘን ማለት ያለአቅሜ ትከሻ መጋፋት እንዳይሆንብኝ ነው)::

በአስመራ ዩኒቨርስቲ ልጆቻቸው እጅግ እንደሚኮሩና ሀገራችንን በምንም አይነት (ከመንግስት ጋር ባንስማማ እንኩዋን) ማገልገል እንዳለብን በአፅንኦት ነግረውኝ ነበር::

ባገኘሁዋቸው ጊዜ አንዳንዴ ምሳ አብሮ የመብላት እድል አጋጥሞኝ ነበር:: በማይጠገበው አንደበታቸው ከሽንኩርት ጋር ያላቸውን "ፀብ" ነግረው አስቀውኛል:: አንድ ጊዜ አአ ከእንግዶች ጋር ሬስቶራንት ገብተው የእሳቸው ምግብ በልዩ ትእዛዝ እንድዘጋጅላቸው ይጠይቃሉ:: ምግቡ ከሌሎች እንግዶቻቸው ጋር አንድ ዐይነት ሆኖ የእሳቸው ግን ሽንኩርት እንዳይገባበት አበክረው ያሳስባሉ:: የእኛ ሀገር ነገር ሆኖ የቀረበላቸው ምግብ ደግሞ (ጥብስ ያሉኝ መሰለኝ) በሽንኩርት ያበደ ነበር:: ከዚያም አስተናጋጁን ይጠሩና በተለመደው ትህትናቸው የእኔ ትዛዝ ያለሽንኩርት እንዲሆንልኝ ነበር ይሉታል:: አስተናጋጁም ይቅርታ ብሎ ምግባቸውን ይዞ ሄዶ ሽንኩርቱን ብቻ ልቅም እድርጎ አውጥቶ ያንኑ ምግብ መልሶ ያመጣላቸዋል:: እኛ የምንገርም ሰዎች አይደለንም ትላላችሁ? 🤔

አለርጂክ ስለሆኑ ሽንኩርት የሚለዩት ገና ከሩቁ (በሽታው) ነው:: በሁዋላ የገባቸው ግን አስተናጋጁ ትእዛዛቸውን በሚገባ ስላላስተላለፈ እንደሚቀጣ ወይንም ሂሳቡን ራሱ እንደሚከፍል ነበር::

ሽንኩርት ተለቅሞ የመጣላቸውን ምግብ ተቀብለው አብሮ የቀረበላቸውን ዳቦ ብቻ በልተው ሌላውን እንዳለ ትተው ሂሳብ ግን በሙሉ ከፍለው ይዎጣሉ:: አስተናጋጁም በጣም አዝኖ የእሳቸውን ሂሳብ ለይቶ ሊመልስላቸው እየሮጠ ይወጣና "እባክዎትን የእርስዎን ሂሳብ እኔ ልክፈል" ይላቸዋል:: ትከሻውን መታ መታ አድርገው ስለ ደግነትህ አመሰግናለሁ:: ሌላ ጊዜ ስመጣ ትጋብዘኛለህ ብለውት እንደሄዱ ነግረውኛል:: እንዲህ አይነት ደግና አርቆ አሳቢ እንዲሁም ከትንሹም ከትልቁም ጋር አብረው መኖር የሚችሉ ሰው መሆናቸውን በድርጊት ጭምር የሚገልፁ ሰው ነበሩ!!

Previous
Previous

የጎሬዋ ያንድ ቀን ፍቅር

Next
Next

የሀይሉ በሶ