አለሙ አሰፋ ሙሉነህ
የዓለሙ አሰፋ ሙሉነህ በጣም አጭር ታሪክ
(አሥመራ ዩኒቨርሲቲ፡- እኤአ 87 ገቢ፣ 91 ወጪ)
ተጻፈ፤ በአበበ አምኃ መንግሥቱ
ኅዳር 22 ቀን 2017 ዓ/ም
ዓለሙና እኔ የአዲስ አበባ ልጆች ነን፤ እሱ ጉለሌ (መድኃኒያለም ት/ቤት ነው የጨረሰው)፣ እኔ ሊሴ ገ/ማርያም ወይም ቴዎድሮስ አደባባይ ጥቁር አንበሳ ት/ቤት፡፡ አሥመራ ዩኒቨርሲቲ ተመድበን በመስከረም ወር 1980 ዓ/ም አንቶኖቭ ስንሳፈር አዲስ አበባ ቦሌ ተገናኝተን ወደ አሥመራ አብረን ተጓዝን፡፡ ላሳሌ ዶርም ተመድበን አንድ ሴሜስተር ቆይተን በሁለተኛው ሴሜስተር ወደዋናው ካምፓስ ዶርም አንድ ተቀየርን፡፡ በአንድ ወቅት ላሳሌ እያለን ሁለታችንም ሳል ታምመን ክሊኒክ ሄደን አንድ ብልቃጥ ካታባዮስ ሽሮፕ ለሁለት ታዝዞልን በየተራ እየተቀባበልን ተጠቅመናል፡፡ ዶርም አንድ እያለን፣ የዓለሙ ድምፅ በጣም ጎርናና ከመሆኑ የተነሳ አንድ የዶርማችን ልጅ ኮፐር ብሎ ቅፅል ስም አወጣለት፤ በአጭሩ ደግሞ ኮፕ ሲባል እሱም ደስ ይለው ነበር፡፡ የኔም ልጆች እስከዛሬ ኮፔ ነው የሚሉት፡፡
በፍሬሽነታችን ላይፍ ሳይንስ አንድ ላይ ተመድበን ነበር፡፡ አንደኛ ዓመት ስንጨርስ ደግሞ እኔ ከ102 ተማሪ ሰቃይ ስለነበርኩ በምርጫዬ፣ ዓለሙ ደግሞ በምደባ ሁለተኛ ዓመት ላይ ማሪን ባዮሎጂና ፊሸሪስ ዲፓርትመንት ገባን፡፡ አሥመራና ምፅዋ ላይ ከሌሎች የዶርምና የክፍል ጓደኞቻችን ጋር የማይረሱ የጨዋና የጎበዝ ተማሪ ትዝታዎችን አሳልፈናል፡፡ ከሌሎች ዲፓርትመንት ልጆች ጋር፣ በተለይም ባዮሎጂዎች ጋር በብዛት እንቀራረብ ነበር፡፡
ዓለሙ የፀባይ ጌታ ስለሆነ ከብዙ ልጆች ጋር በቀላሉ ይግባባ ነበር፡፡ እውነት እውነት እላችኋለሁ አሥመራ እስከገባንበት ጊዜ ድረስ እኔም አሱም አብዛኛውም ተማሪ ስለብሔር ምንነት ምንም ስለማናውቅ ለሁሉም ሰው እኩል ዕይታ፣ በተለይም ደግሞ ለክፍለሀገር ልጆች ልዩ ከበሬታ ነበረን፡፡ አይ ጊዜ!
ሁለተኛና ሦስተኛ ዓመትን ታችኛው ዶርም አሳለፍን፡፡ በ1983 ዓ/ም ምፅዋ ከተያዘች በኋላም ከየካቲት እስከ ሰኔ በሻማ መብራት አጠናን፡፡ ከዚያም በክረምት ሁሉም ተማሪ ወደ አዲስ አበባ እንደተመለስን ዶ/ር ተወልደብርሃን (ፕሬዚደንታችን) በዚያው እንድንቀር አስደረጉ፡፡ አራት ኪሎ ሆነን በአሥመራ ዩኒቨርሲቲ አስተዳደር ሥር አራተኛ ዓመትን አንድ ሴሜስተር ጨረስን፡፡ እኔ ሳባ ዶርም ነበርኩ፡፡ ሁለተኛ ሴሜስተር እንደተጀመረ የብላቴ ዘመቻ ሲመጣ እኔ በዓይን ጤና ችግር ምክንያት ሳላልፍ ስቀር፣ ዓለሙ ብላቴ ሄደና ለመጀመሪያ ጊዜ ተለያየን፡፡ ከብላቴ መልስ መንግሥት ተቀይሮ፣ ሦስት ኤርትራውያን ጓደኞቻችን ወደ አሥመራ ሲሄዱ የቀረነው ዘጠኝ ከመስከረም እስከ ታህሳስ ሁለተኛውን ሴሜስተር ጨርሰን ልደት አዳራሽ ተመረቅን፡፡ ይሁን እንጂ የአሥመራ ዩኒቨርሲቲ ትራንስክሪፕትና ቴምፖራሪ ዘግይቶም ቢሆን ተሰጠን፡፡
ሥራ ስንመደብ ብዙዎቹ ማሪን ባዮሎጂስቶች በጣና ሀይቅ ዙሪያውን ተመድበን ነበር፡፡ ዓለሙ ሰሜን ጎንደር ደልጊ እኔ ደግሞ ደቡብ ጎንደር ወረታ ደረሰን፡፡ ሥራው ግን ቶሎ ቶሎ ያገናኘን ነበር፡፡ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ዓለሙ ወደ ደቡብ ጎንደር ደራ ወረዳ (ሐሙሲት) እንዲቀየር አድርገን ጎን ለጎን ሆነን እንሠራ ነበር፡፡ ሁለታችንም ባለ 200 ሲሲ ሞተር ብስክሌቶችና አንድ የጋራ ባለሞተር ጀልባ ከተሟላ የፊልድ ዕቃ ጋር ተሰጥቶን ነበር፡፡ እኔ ወደ ባህርዳር የዓሣ ምርምር ማዕከል በዕድገት ስዛወር፣ ዓለሙም አብሮኝ ምርምር ይሠራ ነበር፡፡ ባህርዳር እየተመላለሰም ኤሌክትካል ኢንጂነሪንግ ተምሮ ተመርቋል፡፡ ከዚያም ባህር ዳር ጥረት ኢንቨስትመንት በዓሣ እርባታ ባለሙያነት ተቀጥሮ ነበር፤ ቻይና ልከውትም በዓሣ እርባታ ዘጠኝ ወር ሠልጥኗል፡፡ ዓለሙ አንባቢና የትምህርት አቀንቃኝ ነበር!
ከቻይና መልስ ግን ብዙም ሳይቀጥል ሥራ ለቅቆ ወደ አዲስ አበባ ተመለሰ፡፡ ያኔ እኔም አዲስ አበባ ማስተርሴን እየጨረስኩ ስለነበር እንጠያየቅ ነበር፡፡ ከ1993 ዓ/ም ጀምሮ አዲስ አበባ ስንኖር በግል በቤተሰብና በሥራ ቁርኝታችን ጠንካራ ነበር፡፡ ለፒኤችዲ ስዊዘርላንድ ሄጄ ለፊልድ ሥራ ወደ ሀገሬ በየክረምቱ ስመጣ ዓለሙ አብሮኝ ፊልድ ወጥቶ ያግዘኝ ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ አዲስ የመጡ የሶላር ኤነርጂ ቴክኖሎጂዎችን ኢትዮጵያ ውስጥ ያስተዋውቅ የነበረ ቀዳሚው ሰውም ዓለሙ ነበር፡፡ መርካቶ ሱቅ ከፍቶ የማከፋፈልና የኢንስታሌሽን ሥራ በመላው ኢትዮጵያ ይሠራ ነበር፡፡ ከስዊዘርላንድ ጨርሼ እንደተመለስኩ ከአዳማ ዩኒቨርሲቲ አስተማሪነቴና የማማከር ፍቃዴ በተጨማሪ ዓለሙ ለእኔም መርካቶ ከእሱ ሱቅ ጎን ሱቅ አዘጋጅቶልኝ የሶላር ንግድ ፍቃድ አውጥቼ ለተወሰነ ጊዜ እንድሠራ አደረገኝ፡፡ ዓለሙ ለብዙ ሰዎች የሥራ ምንጭ ነበር !
ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ቦታዎች አብረን እየሄድን ሠርተናል፣ ተዝናንተናልም፡፡ ከአዲስ አበባ ከእኔ ሰፈር ከቴዎድሮስ አደባባይና ከእሱ ሰፈር ከጉለሌ ጀምሮ እስከ አሥመራ፣ ምፅዋ፣ ጎንደር፣ ጎርጎራ፣ ደብረታቦር፣ ወረታ፣ አዲስ ዘመን፣ ባህርዳር፣ ጣና ቂርቆስ፣ ዋንዛዬ፣ ናዝሬት፣ ደብረ ዘይት፣ ዝዋይ፣ አዋሳ፣ አሰላ፣ ዲላ፣ አምቦ፣ ወንጪ ሀይቅ፣ ደብረ ብርሀን፣ ደሴ፣ ብዙ ቦታ አይተናል፡፡ በ2010 ዓ/ም ደግሞ ወደ ግብፅ ከመራሁት የንግድ ልዑካን ቡድን ጋር ተካትቶ ከዓለሙ ጋር ከካይሮ እስከ አሌክሳንድሪያ፣ ሜዲትራንያን ባህር፣ አባሳ ወርልድ ፊሽ ሴንተር፣ ታህሪር አደባባይ፣ አባይ ወንዝ ላይና የጊዛ ፒራሚዶች አጠገብ ግመሎች ጋልበን የማይረሱ ጊዜያትን አሳልፈናል፡፡ ከታዋቂ ግብፃዊ የዓሣ ተመራማሪዎችና ትላልቅ የቢዝነስ ሰዎችም ጋር ግንኙነት ፈጥረን ነበር፡፡
ከተወሰኑ ዓመታት በኋላም የሶላር ቢዝነሱ እየተቀዛቀዘ ሲሄድና የኮቪድ ወረርሽኝ ወሬ ሲጀምር አካባቢ፣ ሌላ የሥራ ወዳጁን ለማገዝ የአዲስ ፋብሪካ ቦታ ለማደራጀት ደብረ ብርሃን መግቢያ ጠባሴ አካባቢ ይመላለስ ነበር፡፡ በተጨማሪም ሱሉልታ የመኖሪያ ቤት ሠርቶ እያጠናቀቀ ስለነበር ለብዙ ወራት ተጠፋፍተን ነበር፡፡ በ 2012 ዓ/ም መጋቢት ላይ አንድ ቅዳሜ ቀን ደብረ ብርሃን ይዘኸኝ ሂድ ብሎ ነዳጅ ሞልቶልኝ በእኔ መኪና አብረን ሄድን፡፡ መንገድ ላይ ቆመን የገዛሁትን ባቅላቫ በልተን፣ የፋብሪካውን ቦታ ጎብኝተን፣ ምሳ ጋብዞን፣ ከአምስት ዓይነት አረቄዎች የተከሸነ አረቄ ለኮቪድ መከላከያ ይሁንህ ብሎ በስጦታ ሠጥቶኝ የደርሶ መልሱ ጉዞ ምሽት ላይ ተጠናቀቀ፡፡ እቤቱ አድርሼው የግቢውን በር ከፍቶ ሲገባ አረጋግጬ ወደቤቴ ሄድኩ፡፡ የቅዳሜው ጉዞና ውሎኣችን ስለተመቸው ማክሰኞም አብረን እንድንሄድ ጠይቆኝ በደስታ እሺ አልኩት፡፡ የዚያን ሰሞን ግን በተለየ መልኩ ተቀምጬም ተኝቼም ይጨንቀኝ ነበር፤ አልታመምኩም ግን የምሞት መስሎኝ እረበሽ ነበር፤ ለሰውም አልተናገርኩም፡፡
ሰኞ ምሽት መኪናዬን አዘጋጅቼ ስጨርስ ዓለሙ ስልክ ደውሎልኝ ለነገው ጉዞ ሌላ መኪና ስላዘጋጁለት ‹‹አቤ በቃ አንቺ ቅሪ፣ እኔ ልሂድ›› ብሎኝ ተሰነባበትን፡፡ ‹‹እሺ በሠላም ተመለስ›› ብዬው ስልኩን ዘጋን፡፡ በማግስቱ ማክሰኞ ጧት 3 ሰዓት ላይ ከቤቴ ልወጣ ስል የዓለሙ ባለቤት ስልክ ደውላ የመኪና አደጋ እንደደረሰበት ነገረችኝ፡፡ ሁሉ ነገሬ ተደበላለቀብኝ፡፡ የማደርገውን አጥቼ በቅርቤ የሚኖሩትን ወንድሙንና አባቱን ሄጄ ስጠይቅ ቤተሰቡ፣ ሽማግሌ አባቱም ሁሉም ምስቅልቅላቸው ወጥቷል፡፡ ደብረ ብርሃን ፖሊስ ጋ ደውለን ስንጠይቅ ማረፉን ነገሩን፡፡ በለቅሶና በተሸበረ ሁኔታ ወንድሙን ይዤ ደብረ ብርሃን ስገባ በቅድሚያ የአደጋውን ቦታ አየሁት፤ በጣም ከባድ ነበር፡፡ ጩኸት፣ ለቅሶ፣ ቁጭት፣ እንባ፣…ሁሉም ከንቱ ! የሄደባት ቪትዝ መኪና ሹፌር ኩርባ ላይ አውቶቡስ ደርቦ ሲቀድም ከፊቱ የመጣ ሚኒባስ ገጭቶት ሹፌሩና ዓለሙ ህይወታቸው አለፈ፤ ከኋላ የነበረች ወጣት ኢንጂነር የደህንነት ቀበቶዋም አግዟት በእግዚአብሔር ፈቃድ በመካከለኛ ጉዳት ተረፈች፡፡ የዓለሙን አስከሬን ከፖሊስ ጣቢያ ተረክበን አዲስ አበባ አስመጣን፤ አስኮ ገብርዔልም አሳረፍነው፡፡ ታዲያ በዚያ ሰሞን ተኝቼ እያለሁ የዓለሙ ምስል ይመጣብኝ ነበር፤ ከሳጥኑ ውስጥ ቀና ብሎ ሲቀመጥና መንገድ ላይ በርቀት እየተራመደ ወደጎን ዞሮ ሲያየኝ እመለከት ነበር፡፡
ዓለሙ ለዕውቀት፣ ለንባብ፣ ለሥራ፣ ለማኅበራዊ ህይወት፣ ለቤተሰብ፣ ለጓደኝነት፣ የተጣላን ለማስታረቅ፣ ለፎቶግራፍ፣ ለመዝናናት፣ ተፈጥሮንና ጎበዞችን ለማድነቅ፣ ለሰው ሥራ ለመፍጠር፣ አዳዲስ ሀሳቦችን ለማመንጨት ሲባዝን ዕረፍት ሳያደርግ የኖረ፣ በአጠቃላይ የእውነት ሰው ሆኖ የተፈጠረ ሰው ነበር፡፡ የሚያውቁት ሁሉ ይህን ይመሰክራሉ፡፡ የከፋ በሽታና የሆስፒታል ህክምናም አያውቅም ነበር፡፡ ታዲያ እንዲህ ዓይነት ሰው ለንስሀ እንኳ ሳይበቃ፣ አንድም ሰው እግዚአብሔር ይማርህ ሳይለው፣ ለብቻው ክልትው ብሎ፣ ለዚያውም ደሙ ፈስሶ በወጣበት ሲቀር፣ በተለይም ከእኔ ጋር በተከሰከሰውም የአሥመራ አውሮፕላን ሳንሳፈር ቀርተን፣ ጣና ላይ በከባድ ማዕበል ጀልባችን ስትሰባበርና ስትሰምጥ ተርፈን፣ ከሞተር ብስክሌትና ሌሎችም አደጋዎች ሁሉ ተጠብቀን፣ መጋቢት 2012 ግን በፍቅር ቃል ‹‹አቤ አንቺ ቅሪ፣ እኔ ልሂድ›› ብሎ ሄደ፡፡
ላለፉት ዓመታት በየቀኑ በክርስትና ስሙ ስለነፍሱ መዳን ፀልዬአለሁ፡፡ ለሦስት ዓመታት ሳላውቀው ድባቴ ውስጥ ገብቼ ከሰዎች ጋር ኔትወርክ ማድረግና ሥራ መሥራትም አቁሜ ነበር፡፡ ትምህርት፣ ሥራ፣ ህይወት፣ ተስፋ፣ ጓደኝነትና አብሮነት ሁሉም ከንቱ ሆነውብኝ ነበር፡፡ ከዚያ ወዲህ የስልክ ጥሪዎቼም በጣም ቀነሱ፣ አቆሙም፡፡ ኮቪድም አለፈ፣ መንግሥትም ተቀየረ ተባለ፣ የህዳሴው ግድብም አለቀ፣ የአሥመራ ዩኒቨርሲቲ የቀድሞ ተማሪዎችም ተገናኙ…. ዓለሙ (ኮፔ) ግን የለም! እስከወዲያኛው ላይመለስ ቀረ! ስሙና ሥራዎቹ ግን በቤተሰቡ፣ በጓደኞቹና በስራ ባልደረቦቹ ዘንድ ይኖራሉ፡፡
‹‹አቤ አንቺ ቅሪ እኔ ልሂድ!››
አቤ ቀረ፣ አሌክስ ግን ሄደ!
አሌክስ ወንድማችን እንወድሃለን!
እግዚአብሔር ነፍስህን በገነት ያኑረው፡፡