አሞይ አምለሰትና የካራቬሉ አስተናጋጅ
ለማስታወስና ለመተዋወስ...
የአሥመራ እናቶች "እናትነት" ተዘክሮ የሚያልቅ አይደለም። በብዙዎቻችሁ የሚሰጠው ምስክርነት ሳነብብ እኔ ለመጻፍና ለመግለጽ የሞከርኩት 'ኢምንት' ይሆንብኛል። " ያለውን የሰነዘረ ...." የሚለው ብሂል ይኑርልኝ እንጂ!
ደግነትን፣ ቸርነትን ፣መስጠትን፣ ከአለህ ማካፈል የኢትዮጵያውን ባሕል ነው ቢባልም የአስመራ እናቶች ግን ይለያል።
አንድ ባለ ሱቅ እናት "ደምበኛችን" ነበሩ። "አሞይ!" እንላቸዋለን፣ አሞይ (አምለሰት?) ሱቃቸው እንደማንኛውም ሱቅ ሸቀጦች ብቻ ሳይሆን ለተወሰኑና የተመረጡ "ደንበኞች" የአልኮል መጠጦች አገልግሎት ይሰጣል። እንዳጋጣሚ እኔና ጓደኞቼም የአልኮል መጠጥ የሚቸረቸርባት ክፍል ገብተን የመስተናገድ እድል ነበረን። የመጠጣት ሀሳብና የመጠጫው ገንዘብ ወይም ጋባዡ በአጋጣሚ ወደ አመሻሽ ላይ የተገኘ ከሆነ አማራጩ "አሞይ"ሱቅ ነው። ቪኖ ለመጠጣት።
አሥመራ ከሚመረቱ የአልኮል መጠጦች አንዱ "ቪኖ" ነው። የአሥመራው ቪኖ (ባለ ሰሌኑ ) ዋጋው ሁለት ብር ከሐምሳ /"ከሰባ አምስት" / ነው። የመጠጥ "የማስማት" ደረጃው ከሰው ሰው የተለያየ ነው። "አማካይ" የሚባለው አገላለጽ ይኑርልን። አንድ ጠርሙስ "ቪኖ" ለሶስት ሰው " በመካከለኛ የሞቅታ ከፍታ በመብረር " በጥሩ ጨዋታ የታጀበ ምሽት ለማሳለፍ በቂ ነው/ነበር ።
እዚያ ቤት ስንሄድ አሞይ አምለሰት;
"ይሄ ቪኖ እኮ ከባድ ነው! እናንተ ዩንቨርስቲ የሚሰጠውን ምግብ በልታችሁ እንዴት ትችሉታላች?"
በማለት ከአዘዝነው ቪኖ በፊት እቤታቸው ያላቸውን ምግብ ያቀርቡልን ነበር ። እንጀራ፣ሐንባሻ፣እንጀራ በወጥ በሌላቸው ጊዜ ደግሞ "ቂጫ" ይሰጡን ነበር። ለአንድ ተብሎ ተወጥቶ ሁለት ጠርሙስ የመጠጣት አጋጣሚም ይፈጠራል። ሁለት ቪኖ ለሶስት ሰው ከሞቅታ በላይ በመውሰድ ሙዚቃ ይቀየር ይባላል- ይቀየራል። የአሞይ ጠባብ ቤት ውስጥ ዳንስ ይጀመራል። የአሞይ ፊት ጥይምም አይል። የግቢ መግቢያ ሰአት መድረሱንም የሚያስታውሱን እሳቸው ናቸው።
****
ብዙዎቻችሁ የምታውቁትን "ቡና " አሥመራ ወስዶ መሸጥ እኔም አደርገው ነበር።
አንድ ጊዜ እኔ ቡና ለምሸጥላቸው ለደንበኛዬ " አዲስ አበባዎች ጥሬ ቡና በዝቀተኛ ዋጋ እየገዙ አንዱን ስኒ በአርባ ሳንቲም እየሸጡ እናንተ ግን በውድ ገዝታችሁም አንዱን ስኒ በሃያ አምስት ሳንቲም ብቻ እንዴት ትሸጣላችሁ? በአዲሳባው ዋጋ እንኳን ለምን አትሸጡም? " ብዬ ጠየኳቸው ።
"አዬ ልጄ!" ብለው እንዴት እንደሚገልጹልኝ ጊዜ ወስደው አሰብ አደረጉና " ገዢውስ ማነው? ገዢው በዚህ ጊዜ ገንዘብ ከየት ያገኛል? ከየት ያመጣል? የምናገኘውን ይባርክልን እንጂ በዚህም ተሽጦ ጥሩ ነው በቂያችን ነው ። " ነበር ያሉኝ። ችግርን እና እጥረትን እንደ ምክንያት በመውሰድ የሸቀጦችን ዋጋ በመጨመር ደሃውን ወገን መመዝበር የ"ሐብት" ማከማቻ ዘዴ ሆኖ እያየን ነው። ለአሥመራዎች ግን አይሰራም፣ ይህንንም ነው ያስተማሩን።
ለመውጪያ ;
የአሥመራ ቡና ከትላልቅ ሆቴሎች ውጭ "ውድ " የሚባለው የት እንደሆነ ታስታውሳላችሁ? "ካራቫን" ነበር በውድ የሚሸጠው። " ስንት ነው? "
ሰላሳ ሳንቲም ነው የነበረው። ነገር ግን ቡናቸው ብዙ ፣ብዙ ልዩነት አለው ። የካራቫን ቡና በጣም ወፍራም ነው። ሌላው ልዩነቱ አቀራረቡ ነው፣ በብርጭቆ ሳይሆን በስኒ ነው የሚቀርበው፣ ቤቱም፣ ድባቡም መስተንግዶውም ልዩ ነው። ብዙውን ጊዜ በካምፓስ ተማሪዎች ለምን ተመራጭ እንዳልሆነ አላውቅም፣ ምናልባት የአምስት ሳንቲም ጭማሬው ሊሆን ይችላል። በተለይ ሀይሉ ተስፋዬ ይህንን ቤት ይወደው ነበር፣ ከእስማኤል ሙሳ ጋር ሶስታችን "ደንበኛ" ነበርን። መቀመጫችን አንድ ቦታ ብቻ ነበር። "ለምን? " እዚያ ጠረጴዛ ላይ በሚያስተናግዱቱ ሰው ትህትና ተስበን።
እኚህ አስተናጋጅ የዚያኔ ሀምሳኛ አመት አጋማሽን ያለፉ ይመስለኛል።ጸጉራቸው ሙሉ በሙሉ የተመለጠ፣መካከለኛ ቁመት ያላቸው ቀይ ናቸው። በጣም ትሁት፣ ፈጣን፣ የደንበኞችን ፍላጎት የሚያውቁ፣ የሚረዱና በዚያው ልክ ለማስተናገድ የሚታትሩ ነበሩ። የምንጠጣው ቡና ጠብ ካለች መወልወያቸውን ይዘው ከች ነው። የሶስት ቡና ዋጋው ዘጠና ሳንቲም በመሆኑ አንድ ብር ተሰጥቶ በውብ የሸክላ ስኒ ሰሀን የሚመለሰውን አስር ሳንቲም ለአስተናጋጃችን 'ቲፕ' እንተውላቸው እንደነበርም መጥቀስ ተገቢ ነው። "ሰጠን ወይም እንሰጥ ነበር " አይደለም ጉዳዩ፣ በኋላ ከምነግራችሁ ጉዳይ ጋር ተያያዥ በመሆኑ ነው።
አንድ ጊዜ እኝህ አስተናጋጃችንን ለረዥም ጊዜ አጣናቸው ። ሌላውን አስተናጋጅ ስለ ጤንነታቸው ጠይቀነው ደህንነታቸውን አረጋገጥን። በግምት ከሁለት ወራት በኋላ እኚህ አስተናጋጃችን ተመልሰው አገኘናቸው። ጠበቅ ያለ ሰላምታ ተለዋወጥን፣ የተለመደውን ቡናችንን አዝዘን እየጠጣን በምን ምክንያት ጠፍተው እንደከረሙ ጠይቅናቸው።
"እናንተ አገር፣መሐል አገር ሄጄ ነበር።"
"በደህና ነው?"
"አዎ! እረ በደህና ነው!"
"ዘመድ ለመጠየቅ?"
"አዎ ዘመድ ለመጠየቅም ነው። ዋናው ጉዳይ ግን መኪና ለማሳደስ ነበር"። በመገረም ተውጠን እሳቸውም ወጋቸውን እኛ ደግሞ ማድመጣችንን ቀጠልን። " አዲስ አበባ ቄራ የሚባለው አካባቢ ነው የከረምኩት ። ሁለት ባለ ተሳቢ የጭነት መኪናዎች አሉኝ ። እዚያው በቅርብ ሆኜ ሁለቱንም አጠቃላይ ሞተራቸውን ሰርቪስ ሳስደርግ ከርሜ ነው።" ብለው ነገሩን፣ የካራቫኑ አስተናጋጃችን።
ሁለት የጭነት መኪና ቀርቶ ሁለት ባጃጅ ኖሮት/ኖሮን በተጨማሪነት የመስተንግዶ ስራ ተቀጥሮ የመስራት ሀሳብ ወይም ፈቃደኛነት ያለን ምን ያህሎቻችን ነን?። ስራ ወዳድ፣ ስራ አክባሪዎቹ አሥመራዎች በቃለ-ነቢብ በዩኒቨርስቲ የሚገበየውን እውቀት በተግባር ያሳዩን፣ያስተማሩን ባለውለታዎቻችን ናቸው።
እንደ ምርቃት፣
የካራቫን የቡና ደንበኝነታችን ቀጠለ ፣ቀጠለ፣ ቀጠለ። በኋላ በኋላ ላይ ተስተናግደን ስንወጣ እስማኤል ሙሳ ወደኋላ ዘግየት ማለት አመጣ። ተከታተልኩት፣ ተከታተልኩት። አንድ ብር ተከፍሎ በስኒ ማስቀመጫ የሚመጣውን እና ለአስተናጋጃችን የምንተወውን የአስር ሳንቲም መልስ እስማኤል አንስቶ እንደሚወስድ ደረስኩበት።
" ሁለት ባለ ተሳቢ የጭነት መኪና ላለው ሰው እኛ የአስር ሳንቲም ቲፕ መስጠት የለብንም ። ሰሞኑን እኮ ከዚህ እንደወጣን ሲጋራ የምገዛልህ ቲፗን እያነሳሁ ነው። ሀይሉ እንዳይሰማ! ነበር የሰጠኝ ምላሽ። " እኛ የምንሰጣቸው የአስር ሳንቲም ቲፕ እና ከእሳቸው ሁለት የጭነት መኪና ባለቤትነት ጋር ግንኙነት የለውም፣ ሊኖረው አይገባም " የሚል ሀሳብ በአእምሮዬ ሽው ቢለኝም የሚገዛልኝ ሲጋራ አመዘነብኝ።