የካምፓሱ አመፅና ውጤቱ..

1. ላሳሌን በኔቪ ተቀምተን ከአብዮት አደባባዩ ሁዋላ ማይ ጩኸት የሚባል ሰፈር ኔቪ የለቀቀው ካምፕ በመግባታችንና በጣም እሩቅ ስለነበር አንማርም ብለን ስለነበር ጉዋድ ካሳዬ አራጋው የመጡት:: ብዙ ቢያስፈራሩንም በፍጥነት ቻው ሆቴል እና ገማግል አስገቡን:: ቅርብ ቦታ- ከላሳሌም የቀረበ::

2. ⁠1982ዓም ጦርነቱ ጦፎ ህዝቡ ወደ መሀል አገር እየጎረፈ ስለነበር ግንቦትና ሰኔ ትኬት ለመቁረጥ ስንሞክር እስከ መስከረምና ጥቅምት ቡክ ሆኖ ነበር:: ከግራጁዌሽን በሁዋላ ነገር ተባባሰ የውሀ እጥረትም ተከሰተ:: ተማሪው በሞላ በትራንስፖርት እጦት ስታክ አደረገ:: አንድ ነገር ማድረግ አለብን ብለን የተወሰንን ጉዋደኛሞች እቅድ አውጣን:: አመፅ ማቀናበር ፋኔ ነበር መሰለኝ:: ማታ ላይ ቻው ሆቴል ላሉ ተማሪዎች በሞላ በአካል ለእያንዳንዱ በየዶርሙ እየዞርን ነገ ሜይን ካምፓስ እንደሚዘጋና ማንም እንዳይገባና የምግብ አድማም እንድሚኖር ነገርን:: ለመንግስት ምክር ቤት ለጉዋድ መንግስቱ ኃይለማርያም በአድራሻ የተፃፈ ደብዳቤ ተረቀቀ:: በየሸዋሉል ስዕል የመሰለ የእጅ ፅሁፍ በአራት ወይም አምስት ቅጂ ተፅፎ አደረ:: በነጋታው ሜይን ካምፓስን ተቆጣጠርነው:: መግቢያው ላይ ያለው ደረጃ ላይ ተማሪው ሁሉ ቦታውን ያዘ:: አስተባባሪዎቹ ካፌው መዘጋቱን አረጋገጥን (ያልሰሙ ጥቂት ተማሪዎችና መሳተፍ ያልፈለጉ ሁለት የአኢወማ አመራሮች ቁርስ እየበሉ ነበር) :: እነሱን እንዲያቁዋርጡ እርገን ወጣን:: ብርሀኔ መስፍን (በወቅቱ የነበረው አመለ ሸጋው ስቱደንት ዲናችን )በጠዋት ገብቶ ቢሮው ውስጥ አገር አማን ብሎ ስራ ላይ ነበር:: አንዳንዴ ብር የምፈልጠው ወዳጄ ነበርና ሁኔታውን አስረድቼው ከቢሮው ወጥተን ከግቢ እንዲውጣ ዋናው ህንፃ ደረጃጋ ከመድረሳችን በፊት የተማሪውን መፈክርና ጩኸት ሲሰማ ፈርቶ በመሀላቸው አልወጣም አለ:: ቃል ገብቼ አይዞህ ብዬ ለተማሪዎቹም ምንም እንዳይሉት ነግሬ ይዤው ወጣሁ በተማሪው መሀል ሲያልፍ ግን ያመንኩዋቸው ጉዋደኞቼ 'ሌባ ሌባ' ማለት ጀመሩ :: ብርሀኔ ደንግጦ ጆሮውን ይዞ በፍጥነት ከግቢ ወጣ::

እንደምንም ጩኸቱን አስቁሜ የተጻፈውን ደብዳቤ አነበብኩና ተማሪው ለደብዳቤው ይዘት ድጋፉን በጩኸት ደገፈ:: የደብዳቤው መዝጊያ '... ትራንስፖርት ቀርቦልን የማታነሱን ከሆነ በውሀ ጥም ከምንሞት በቀበሮ ጉርጉዋድ ሆኖ እግሩ ሲመታ ልባችን የሚደማለት ሰራዊትጋ ቀላቅሉንና ጥይት አብርደንም ቢሆን እንሙት' የሚል የማባቢያ ቃላት ነበሩበት:: ጩኸቱ ጋብ እንዳለም 'በሉ ይሄ ደብዳቤ በእስቸኩዋይ የአደራ ደብዳቤ የሚላክ ስለሆነ ያላችሁን አዋጡ ብዩ እኔና ጉዋደኛዬ መንክር ጥበቡ መሰብሰብ ጀመርን:: ሁሉም ሳንቲም እጃችን ላይ ጣለ (ብር የለም)::

ይህ ሲሆን ግቢው በደህንነቶችና በወታደሮች ተከቡዋል:: ሰው አይገባም አይወጣም:: የያዝነው ሳንቲም ተቆጠረ 23 ብር ከ60 ሳንቲም:: ከዛ ተማሪው ሁሉ እዛው እንዲጠብቀንና ማንም ግቢውም እንደተዘጋ እንዲቆይ ተስማምተን እኔና መንክር ወደ ፓስታ ቤት:: ስንወጣ ሁሌም ደህንነታችን የሚያሳስባቸው የአካባቢው ነዋሪዎች በብዛት አካባቢውን ከበዋል:: የኛን መውጣት ሲያዩ ደህንነታችንን ይጠይቁን ነበር::

በ30 ደቂቃ ውስጥ ፖስታውን በ15 ብር ልከን ተመለስን::

ተመልሰን ከተማሪውጋ ተቀላቅለን መግቢያውን እንደተቆጣጠርን መጠበቅ ጀመርን:: ወዲያው ካሳዬ አራጋው ከተወሰኑ ጀነራሎችጋ በወታደር ታጅበው መጡ:: በሩ እንደተዘጋ ነበር (ካምፓስ ፖሊሶቹም ያግዙን የለ):: ጉዋድ ካሳዬ እንግባና አናግሩን አሉ እሱና ጀነራሎቹን አስገብተን በሩ ተዘጋ:: በውስጥ በኩል በሩጋ እንድቆሙ የተላከውን ደብዳቤ ቅጂ በጃቸው ለሶስቱም ሰጠሁዋቸው:: ባለሶስት ገፅ ስለነበር ጉዋድ ካሳዬ ገልበጥ ገልበጥ አርጎ አየና በሁዋላ አነበዋለሁ እናንተ ባጭሩ ንገሩኝ አለና እኔም አንድ ሁለት ተማሪዎችም ተናገርን:: ዋናው ሀሳብ ውሀ የለም የውሀ ቦቲያችን ለሌላ ቦታ ያከፋፍላል (ላሜ ቦራ ይሉዋታል) ለኛ ግንአያመጣም ሽንት ቤቶች ቆሽሸዋል ጫካ እንዳንሄድ በቦንብ ታጥሩዋል ካፌም በአግባቡ ለመስራት እየተቸገረ ነው ትራንስፓርት የለም ስለዚህ መንግስት ትራንስፖርት መድቦ ይውሰደን የሚል ነበር::

ካሳዬ አራጋውም 'ጥያቄያችሁ አግባብነት አለው መንግስት ትራንስፖርት ያቀርባል ለማንኛውም ለዛሬ ይብቃችሁ የዛሬ ሶስት ቀን እዚሁጋ ጠብቁኝ መልስ ይዤ እመጣለሁ አሉን:: እኛም ለስኬታማው ትግላችን ተመሰጋግነን ከሶስት ቀን በሁዋላ እንደዚሁ በሩን ዘግተን ለመጠበቅ ተስማምተን ተበተንን:: ብዙዎቻችን ከግቢ ስንወጣ ባለስልጣኖቹም ወደየመኪናቸው እየሄዱ ነበርና አንዱ የፖሊስ ጀነራል በወታደር አስጠራኝ: የልቤ ምት ፍጥነቱዋን ጨመረች አጠገቡ ስደርስ ግን ደስ በሚል ፈገግታ እያየኝ ግበዝ ጎረምሳ ነሽ እያለ ፀጉሬን አሻሸኝና ወዴት እየሄዳቹህ ነው አላኝ ቁርስ አልበላንም ወደሻይ ቤት አልኩት:: አይዙዋቹህ ብሎኝ ወደ ላንድ ክሩዘሩ ገባ:: ማስጠንቀቂያ ይሁን ምን እስካሁን አልገባኝም::

እኔና ጉዋደኞቼም ከፖስታ መላኪያ የተረፈውን 7ብር ከ60 ይዘን አንዱ ላቴሪያ ገብተን ፉላችንን አጣጣምን!

በሶስተኛው ቀን ግን በጠዋት ካፌ ስንሄድ ከካፌው ፊትለፊት ያሉ ዶርሞች በረንዳ ላይ ያላው ለወትሮው ብር የመጣላቸው ዝርዝር የሚለጠፍበት ቦርድ ላይ አዲስ ማስታወቂያ ተለጥፎዋል:: ከሚቀጥለው ቀን ጀምሮ ብሶስት ቀን ውስጥ ሁላችንንም በኢትዮጵያ አየር መንገድ የሚያነሳ የበረራ ፕሮግራም! ግቢው በደስታ ተቀወጠ:: የመጀመሪያዎቹ በረራዎች የግራጅዌቲንግ ክላስ ነበር:: በሚቀጥለው ቀን በመጀመሪያው በረራ እኔና ጉዋደኞቼ በረርን!...አስመሪኖ ባይ ባይ ....

ከዛ በሁዋላ ያለውን .....እኔ አልነበርኩም....

Previous
Previous

ዶ/ር ጌታቸው ቦሎድያ በአስመራ

Next
Next

ስንቱ ስንቱ......ይታወስ